1 የሜዶናዊው የአርጤክስስ ልጅ ዳርዮስ በባቢሎን በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት 2 በዘመነ መንግሥቱ በመጀመሪያው ዓመት፣ እኔ ዳንኤል ለነቢዩ ኤርምያስ በተሰጠው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት፣ የኢየሩሳሌም መፈራረስ ሰባ ዓመት እንደሚቆይ ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተዋልሁ። 3 ስለዚህ ማቅ ለብሼ በራሴም ላይ ዐመድ ነስንሼ በጾምና በጸሎት፣ በምልጃም ፊቴን ውደ ጌታ አምላክ አቀናሁ። 4 ወደ እምላኬ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፣ ተናዘዝሁም፤ “ከሚወዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ሁሉ ጋር የፍቅር ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ጌታ ሆይ፤ 5 እኛ ኃጢአት ሠርተናል፣ በድለናልም፣ ክፋትን አድርገናል፣ ዐምፀናልም፣ ከትእዛዝህና ከሕግህ ዘወር ብለናል። 6 ለንጉሦቻችን፣ ለልዑሎቻችንና ለአባቶቻችን እንዲሁም ለምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በአንተ ስም የተናገሩትን አገልጋዮችህን ነቢያትን አልሰማንም። 7 “ጌታ ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ነገር ግን በአንተ ላይ ስለ ሠራነው ታላቅ ክፋት እኛን በበተንህባቸው አገሮች ሁሉ የምንገኝ የይሁዳ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌምና የመላው እስራኤል ሕዝብ፣ በሩቅም ሆነ በቅርብ ያለን በዚህ ቀን ኀፍረት ተከናንበናል። 8 እግዚአብሔር ሆይ፤ እኛና ንጉሦቻችን፣ ልዑሎቻችንና አባቶቻችን በአንተ ላይ ኃጢአት ስለ ሠራን ኀፍረት ተከናንበናል። 9 ምንም እንኳ በእርሱ ላይ ያመፅን ብንሆን፣ ጌታ አምላካችን ይቅር ባይና መሐሪ ነው። 10 እግዚአብሔር አምላካችንን አልታዘዝነውም፤ ደግሞም በአገልጋይቹ በነቢያት በኩል የሰጠንን ሕግ አልጠበቅንም፤ 11 መላው እስራኤል አንተን ባለመታዘዝ ሕግህን ተላልፎአል፤ ዘወርም ብሎአል።በአንተ ላይ ላይ ኃጢአትን ስለ ሠራን፣ በእግዚአብሔር አገልጋይ በሙሴ ሕግ የተጸው መሐላና ርግማን ፈሰሰብን። 12 ታላቅ ጥፋት በእኛ ላይ በማምጣት፣ የተነገረውን ቃል ፈጸምህብን፤ በኢየሩሳሌም ላይ የተደረገውን የሚያህል ከሰማይ በታች ከቶ የለም። 13 በሙሴም ሕግ እንደ ተጻፈው፤ ይህ ሁሉ ጥፋት በእኛ ላይ ደረሰ፤ ሆኖም ከኃጢአታችን በመመለስና እውነትህን በመከተል ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ምሕረትን አልፈለግንም። 14 አምላካችን እግዚአብሔር በሚያደርገው ሁሉ ጻድቅ ነውና፣ በእኛ ላይ እግዚአብሔር ጥፋት ከማምጣት አልተመለሰም፣ እኛም አልታዘዝነውም። 15 አሁንም ሕዝብህን ከግብፅ ምድር በብርቱ እጅ ያወጣህ፣ እስከዚህም ቀን ድረስ ስምህ እንዲታወቅ ያደረግህ፤ ጌታ አምላካችን ሆይ፤ ኃጢአት ሠርተና፣ አንተንም በድለናል። 16 ጌታ ሆይ እንዳደረግኸው የጽድቅ ሥራህ ሁሉ፣ ከከተማህ ከኢየሩሳሌም፣ ከቅዱሱም ተራራህ ቁጣህን መልስ፣ በእኛ ኃጢአትና በአባቶቻችን በደል ምክንያት ኢየሩሳሌምና ህዝብህ በዙሪያችን ባሉት ዘንድ መሣለቂያ ሆነዋል። 17 አሁንም አምላካችን ሆይ፣ የአገልጋይህን ጸሎትና ልመና ስማ። ጌታ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል ፊትህን ወደፈረሰው መቅደስ መልስ። 18 አምላክ ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፣ ዐይንህን ገልጠህ መጥፋታችንንና ስምህ የተጠራበትን ከተማ ተመልከት። ልመናችንን የምናቀርበው ስለ ጽድቃችን ሳይሆን፣ ስለ ታላቅ ምሕረትህ ነው። 19 ጌታ ሆይ፣ አድምጥ! ጌታ ሆይ፤ ይቅር በል! ጌታ ሆይ፤ ስማ! አድርግም፤ ስምህ በከተማንህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና አምላኬ ሆይ፣ ስለ ስምህ ስትል አትዘግይ።” 20 እኔም እየተናገርሁና እየጸለይሁ፣ የራሴንና የሕዝቤን የእስራኤልን ኃጢአት እየተናዘዝሁ፣ ስለ ቅዱስ ተራራውም እግዚአብሔር አምላኬን እየለመንህ 21 እየጸለይሁም ሳለሁ፣ በመጀመሪያው ራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል፣ በሠርክ መሥዋዕት ጊዜ በፍጥነት እየበረረ ወደ እኔ መጣ። 22 እርሱም እንዲህ ብሎ አስረዳኝ፤ “ዳንኤል ሆይ፣ አሁን ጥበብንና ማስተዋልን ልሰጥህ መጥቻለሁ 23 አንተ እጅግ የተወደድህ ስለሆንህ፣ ገና መጸለይ ስትጀምር መልስ ተሰጥቶአል፣ አኔም ይህን ልነግርህ መጣሁ። ስለዚህ መልእክቱን ልብ በል፤ ራእዩንም አስተውል። 24 ዐመፃን ለማስቆም፣ ኃጢአትን ለማስወገድ፣ በደልን ለማስተሰረይ፣ ዘላለማዊ ጽድቅን ለማምጣት፣ ራእይንና ትንቢትን ለማተምና እጅግ ቅዱስ የሆነውን ለመቀባት ስለ ሕዝብህና ስለ ተቀደሰችው ከተማህ ሰባ ሱባዔ ታውጇል። 25 ይህንን ዕወቅ አስተውለውም፤ ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ገዢው መሲሕ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስልሳ ሁለት ሱባዔ ይህናል። ኢየሩሳሌም ከጎዳናዎቿና ከቅጥሮቿ ጋር ትታደሳለች፤ ይህ የሚሆነው ግን በመከራ ጊዜ ነው።