ምዕራፍ 8

1 ንጉሥ ቤልሻዘር በነገሠ በሦስተኛው ዓመት አስቀድሞ ከተገለጠልን ራእይ በኋላ እኔ ዳንኤል ሌላ ራእይ አየሁ። 2 በራእዩም በኤሳም አውራጃ በሱሳ ግንብ ራሴን አየሁት፤ በራእዩም በኡባል የውሃ መውረጃ አጠገብነበርሁ፤ 3 ዓይኔን አንስቼ ስመለከት እነሆ፣ ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራ በግ በወንቁ አጠገብ ቆሞ አየሁ፤ ቀንዶቹም ረጃጅሞች ነበር፤ ከቀንዶቹም አንዱ ከሌላው ይረዝማል፤ ረጅሙ ቀንድ የበቀለው ዘግይቶ ቢሆንም ከአጭሩ ይልቅ በርዝመቱ የላቀ ነበር። 4 አውራ በጉም ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ በቀንዱ ሲጎሽም አየሁ። ምንም ዐይነት እንስሳ ሊቋቋመው አልቻለም፤ ከእጁም ሊያድን የሚችል አልነበረም፤ የፈለገውን ሁሉ አደረገ፤ ታላቅም ሆነ። 5 ስለዚህ ነገር እያሰብሁ ሳለሁ፣ በዐይኖቹ መካከል ትልቅ ቀንድ ያለው አውራ ፍየል፣ መሬት ሳይነካ ምድርን ሁሉ እያቋረጠ በድንገት ከምዕራብ መጣ፤ 6 በወንዙ አጠገብ ቆሞ ወዳየሁት፣ ሁለት ቀንድ ወዳለው አውራ በግ ተንደርዶ መጣበት፤ በታላቅ ቁጣም መታው። 7 እየወጋውና ሁለቱን ቀንዶቹን እየሰበረ፣ በጭካኔ አውራውን በግ ሲጎዳው አየሁ፤ አውራ በጉም ለመቋቋም ጉልበት አልነበረውም። ፍየሉ በምድር ላይ ጥሎ ረገጠው፤ አውራ ብጉንም ከፍየሉ እጅ ለማዳን የሚችል አልነበረም። 8 ፍየሉም ታላቅ ሆነ፤ ነገር ግን በኃይሉ በበረታ ጊዜ፣ ትልቁ ቀንዱ ተሰበረ፤ በቦታውም ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት የሚያመለክቱ አራት ታላላቅ ቀንዶች በቀሉ። 9 ከእነዚህም ቀንዶች መካከል በአንዱ ላይ አንድ ትንሽ ቀንድ በቀለ፤ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ተከበረችው የእስራኤል ምድር በኃይል አደገ። 10 ከሰማይ ሠራዊት ጋር ጦርነት እስኪገጥም ድረስ አደገ፤ ከሰማይና ከክዋክብት ሠራዊት የተወሰኑትን ወደ ምድር ጣለ፣ ረጋገጣቸውም። 11 ከሰማይ ሠራዊት አለቃ ጋር እስኪተካከል ድረስ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ የልዑሉንም የዘወትር መሥዋዕት ወሰደበት፤ የመቅደሱንም ስፍራ አረከሰ። 12 ከዐመፅ የተነሳም የቅዱሳን ሠራዊት ለፍየሉ ቀንድ አልፎ ተሰጠ፤ የሚቃጠል መሥዋዕቱም እንዲቆም ተደረገ። እውነትን ወደ ምድር ይጥላል የሚያደርገውም ሁሉ ይከናወንለታል። 13 ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ሌላውም ቅዱስ እንዲህ አለው፤ “ስለ ዘወትሩ መሥዋዕት፣ ለጥፋት ምክንያት ስለሆነው ዐመፅ፣ ከእግር በታች እንዲረገጡ ዐልፈው ስለሚሰቱት መቅደስና ሠራዊት የታየው ራእይ የሚፈጸመው መቼ ነው?” 14 እርሱም፣ “እስከ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ምሽቶችና ማለዳዎች ድረስ ይቆያል፤ ከዚያም መቅደሱ እንደገና ይነጻል” አለኝ። 15 እኔ ዳንኤል ራእዩን ስመለከትና ሳስተውል ሳለ፣ ሰውን የሚመስል ከፊት ለፊቴ ቆመ፤ 16 ከኡባልም፣ “ገብርኤል ሆይ፤ ለዚህ ሰው የራእዩን ትርጕም ንገረው” ብሎ የሚጮህ የሰው ድምፅ ሰማሁ። 17 እኔ ወደቆምሁበት እየቀረበ ሲመጣ፣ ደንግጬ በግንባሬ ተደፋሁ፣ እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ራእዩ ስለ ዘመኑ ፍጻሜ እንደሆነ አስተውል” አለኝ። 18 እየተናገረኝ ሳለ፣ በምድር ላይ በግንባሬ ተደፋሁ፤ በከባድ እንቅልፍም ተዋጥሁ፣ እርሱ ግን ዳሰሰኝና በእግሮቼ አቆመኝ። 19 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ራእዩ በመጨረሻው ዘመን ሊሆን ያለውን የሚያመለክት ስለሆነ፣ በኋላ በቁጣው ዘመን ምን እንደሚሆን እነግርሃለሁ። 20 ያየኸው ሁለት ቀንዶች የነበሩት አውራ በግ፣ የሜዶንና የፋርስን መንግሥታት ያመለክታል። 21 ተባዕቱ ፍየል የግሪክ ንጉሥ ሲሆን፣ በዐይኖቹም መካከል ያለው ትልቁ ቀንድ የመጀመሪያው ንጉሥ ነው። 22 የተሰበረውን ቀንድ የተኩት አራቱ ቀንዶቹ፣ ከመንግሥቱ የሚወጡትን አራት መንግሥታትን ያመለክታሉ፣ ነገር ግን ከእርሱ ጋር የሚተካከል ኃይል አይኖራቸውም። 23 “በዘመነ መንግሥታቸው በስተ መጨረሻ፣ ዐመፀኞች ፍጹም እየከፉ በሚሄዱበት ጊዜ፣ አስፈሪ ፊት ያለው አታላይ ንጉሥ ይነሣል። 24 እጅግ ብርቱ ይሆናል፤ ነገር ግን በገዛ ኃይሉ አይደለም። አሠቃቂ ጥፋት ይፈጽማል፤ የሚያደርገው ሁሉ ይከናወንለታል፤ ኃያላን ሰዎችንና ቅዱሳኑን ሕዝብ ያጠፋል። 25 እጅግም ተንኮለኛ ስለሆነ በማታለል ይበለጽጋል፤ በልዑላን ልዑልም ላይ ይነሣል፤ ይሁን እንጂ እርሱም ይጠፋል ነገር ግን በሰው ኃይል አይደለም።