1 የፋርስ ንጉስ ቂሮስ በነገሰ በሦስተኛው ዓመት ብልጣሶር ለተባለው ዳንኤል ራዕይ ታየው መልዕክቱ እውነት ነው፤ ስለ ታላቅ ጦርነትም የሚገልፅ ነበር፡፡ መልእክቱንም ይገነዘብ ዘንድ በራዕዩ ማስተዋል ተሰጠው፡፡ 2 በዚያ ጊዜ እኔ ዳንኤል ለሦስት ሳምንት አለቀስኩ፤ 3 ሦስቱም ሳምንት እስኪፈፀም ድረስ ጥሩ ምግብ አልበላሁም፤ ስጋም ሆነ የወይን ጠጅ ወደ አፌ አልገባም፤ ቅባትም አልተቀባሁም፡፡ 4 በመጀመሪያው ወር አያ አራተኛው ቀን፤ በታላቁ በጤግሮስ ወንዝ ዳር ቆሜ፤ 5 ቀና ብዬ ስመለከት፣ በፊቴ በፍታ የለበሰ እና በወገቡም ላይ ምርጥ የወርቅ ቀበቶ የታጠቀ አንድ ሰው አየሁ፡፡ 6 አካሉ እንደ እንቁ፣ ፊቱ እንደ መብረቅ፣ ዐይኖቹ እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹ እንደ ጋለ ናስ የሚያብረቀርቁ ድምፁም እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበር፡፡ 7 7 ራዕዩን ያየሁት እኔ ዳንኤል ብቻ ነበርሁ፤ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች አላዩም፤ ነገር ግን ታላቅ ፍርሃት ስለ ወደቀባቸው ሸሽተው ተደበቁ፡፡ 8 ስለዚህ ይህን ታላቅ ራዕይ እያየሁ ብቻዬን ቀረሁ፤ ምንም ጉልበት አልነበረኝም፤ መልኬ እጅጉን ገረጣ፤ ኃይልም አጣሁ፡፡ 9 ከዚያም የቃሉን ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ፣ በግንባሬ በምድር ላይ ተደፍቼ በከባዱ እንቅልፍ ተኛሁ፡፡ 10 እነሆም አንድ እጅ ዳሰሰኝ፤ እየተንቀጠቀጥሁም በእጄና በጉልበቴ አቆመኝ፤ 11 እርሱም፤ “ እጅግ የተወደድህ ዳንኤል ሁይ፣ አሁን ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን አስተውል፤ ቀጥ ብለህም ቁም አለኝ፡፡ ይህን ሲለኝም፤ እየተንቀጠቀጥሁ ተነስቼ ቆምሁ፡፡ 12 ደግሞም እንዲ አለኝ፤ “ዳንኤል ሁይ፣ አትፍራ ማስተዋልን ለማግኘትና በአምላክህም ፊት ራስህን ለማዋረድ ከወሰንክበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ ቃልህ ተሰምቷል፤ እኔም የቃልህን መልስ ይዤ መጥቻለሁ፡፡ 13 ነገር ግን የፋርስ መንግስት አለቃ ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል ሊረዳኝ ወጣ፡፡ 14 ራዕዩ ሊፈፀም ገና ብዙ ዘመን ስለሚቀረው ወደፊት በህዝብህ ላይ የሚሆነውን ልገልፅልህ አሁን ወደአንተ መጥቻለሁ፡፡” 15 15 ይህን እየተናገረኝ ሳለ፣ ፊቴን ወደ ምድር አቀረቀርሁ፣ የምናገረውንም አጣሁ፡፡ 16 ከዛም የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሮቼን ዳሰሰ፣ እኔም አፌን ከፈትኩ፣ መናገርም ጀመርኩ፤ በፊቴ የነበረውንም እንዲህ አልኩት፤ “ ጌታዬ ሆዬ ከራዕዩ የተነሳ ተሰቃይቻለሁ ሃይልም አጣሁ፤ 17 ጉልቤቴ ከዳኝ፤ መተንፈስም አቅቶኛል፣ እኔ አገልጋይህ ከአንተ ጋር መነጋገር እንዴት እችላለሁ?” 18 እንደገናም ሰው የሚመስለው ዳሰሰኝ አበረታኝም፡፡ 19 እርሱም፤ “እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፤ አትፍራ፤ ሰላም ላንተ ይሁን፤ በርታ፤ ፅና” አለኝ፡፡ እየተናገረኝም ሳለ፣ በረታሁና፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አበረትተኸኛልና ተናገር” አልሁት፡፡ 20 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ለምን ወደ አንተ እንደ መጣሁ ታውቃለህ? የፋርስን መንግሥት ለመውጋት እመለሳለሁ፤ እኔም ስሄድ የግሪክ አለቃ ይመጣል። 21 አስቀድሜ ግን በእውነት መጽሐፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ ከእነዚህ አለቆች ጋር ለመዋጋት ከአለቃችሁ ከሚካኤል በስተቀር የሚረዳኝ የለም።