1
ልያ ለያዕቆብ የወለደችለት ሴት ልጅ ዲና፤ አንድ ቀን የዚያን አገር ሴቶች ለማየት ወጣች።
2
የአገሩ ገዥ የኤዊያዊ የኤሞር ልጅ ሴኬም ባያት ጊዜ ያዛት በማስገደድም ክብረ ንጽሕናዋን ደፈረ።
3
ልቡ በያዕቆብ ልጅ በዲና ተማረከ፤ ልጅቷንም በጣም ወደዳት፤ በጣፈጠም አንደበት አናገራት።
4
ሴኬምም አባቱን ኤሞርን፣ “ይህችን ልጅ አጋባኝ” አለው።
5
ያዕቆብ የልጁን የዲናን ክብረ-ንጽሕና ሴኬም እንደደፈረ ሰማ፤ ነገር ግን ወንዶች ልጆቹ የከብት መንጋ ይዘው ተሰማርተው ስለነበር፣ እነርሱ እስኪመጡ ዝም ብሎ ቆየ፤
6
ከዚያም የሴኬም አባት ኤሞር፣ ያዕቆብን ሊያነጋግረው ወጣ።
7
የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም የተፈጸመውን ድርጊት እንደሰሙ ወዲያውኑ ከመስክ መጡ፤ ሴኬም መደረግ የማይገባውን አስነዋሪ ነገር በእስራኤል ላይ በመፈጸም የያዕቆብን ልጅ ስለደፈረ አዘኑ እጅግም ተቆጡ።
8
ኤሞር ግን እንዲህ አላቸው፤ “ልጄ ሴኬም ልጃችሁን በጣም ወዶአታል፤ ስለዚህ እንዲያገባት ፍቀዱለት፤
9
በጋብቻ እንተሳሰር፣ ሴት ልጃችህን ስጡን፣ የእኛንም ሴቶች አግቡ።
10
አብራችሁንም መኖት ትችላላችሁ፤ አገራችን አገራችሁ ናት፣ ኑሩባት፤ ነግዱባት፣ ሀብት ንብረትም አፍሩባት።
11
ሴኬም ደግሞ የዲናን አባትን ወንድሞች እንዲህ አላቸው። “በእናንተ ዘንድ ሞገስ ላግኝ እንጂ የተጠየቅሁትን ሁሉ እሰጣለሁ፤
12
ለሙሽራዋም ጥሎሽ የፈለጋችሁትን ያህል ጠይቁኝ፤ እርሷን እንዳገባ ፍቀዱልኝ እንጂ፣ የፈለጋችሁትን ሁሉ ለመጠት ዝግጁ ነኝ።”
13
ሴኬም እኅታቸውን ዲናን አስነውሮ ስለነበር የያዕቆብ ልጆች ለእርሱና ለአባቱ በተንኮል እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፣
14
እንዲህ አሉአቸው፤ “እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ብንሰጥ ውርደት ስለሚሆንብን፣ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም።
15
ሆኖም የምንስማማበት አንድ መንገድ ብቻ አለ፤ ይኸውም አንተና በእናንተ ዘንድ ያሉት ወንዶች ሁሉ እንደኛ የተገረዛችሁ እንደሆነ ነው።
16
እንዲህ ከሆነ እናንተ የእኛን ሴቶች ልጆች ታገባላችሁ፣ እኛም የእናንተን ሴቶች ልጆች እናገባለን፣ አንድ ሕዝብ ሆነንም አብረን እንኖራለን።
17
ዐሳባችንን ባትቀበሉና ባትገረዙ ግን እኅታችንን ይዘን እንሄዳለን።