1 ይህ የንጉሥ ሰለሞን እጅግ ድንቅ መዝሙር ነው። 2 ከንፈሬን ሳመኝ፡ምክንያቱም ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ደስ ይለኛል። 3 የተቀባኽው ሽቶ መዓዛው እጅግ መልካም ነው። ክብርህ እጅግ ታላቅ ሲሆን፡ልክ እንደ ተቀባኽው የሽቱ መዓዛም የሚናኝ ነው። ሌሎች ቆነጃጅት በአንተ የተማረኩትም ከዚህ የተነሳ ነው። 4 ፍጠን፡ወደቤትህም ይዘኽኝ ሂድ። እርሱ ለእኔ እንደ ንጉሥ ነው፡ወደ መኝታ ክፍሉም አመጣኝ። በአንተ በጣም ደስ ይለኛል፡ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ያስደስታል። ሌሎች ቆነጃጅት አንተን ማፍቀራቸው ትክክል ነው። 5 እናንት የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት እኔ ጥቁር ነኝ፡ ይሁን እንጂ ውብ ነኝ። ጥቁረቴም እንደ ቄዳር ድንኳኖች ወይም እንደ ሰለሞን ቤተ መቅደስ ውብ መጋረጃዎች ነው። 6 ይሁን እንጂ ትኩር ብላችሁ አትመልከቱኝ፡ ምክንያቱም መልኬን ያጠቆረው ፀሐይ ነው። ወንድሞቼ ስለተቆጡኝ በፀሓይ በወይን ተክል ቦታዎች ውስጥ እንድሠራ አስገደዱኝ። ስለዚህ የራሴን ሰውነት መንከባከብ አልቻልኩም። 7 ውዴ ሆይ፡ዛሬ የበጎችህን መንጋ የምታሰማራው የት ነው? በቀትርም የት እንደምታሳርፋቸው እስቲ ንገረኝ። ይህን ማወቅ እሻለሁ፡ ምክንያቱም የጓደኞችህ መንጎች በሚሰማሩበት ስፍራ ሁሉ እንደ ሴተኛ አዳሪ አንተን ፍለጋ መንከራተቴ ተገቢ አይደለም። ሙሽራው 8 አንቺ ከሴቶች ሁሉ ይበልጥ እጅግ የተዋብሽ ሆይ፡ እኔን የምትፈልጊና በጎቼን ዬት እንደማሰማራ የማታውቂ ከሆነ፥የበጎቹን ዱካ ተከተዪ፡የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞች ድንኳን አጠገብ አሰማሪ። 9 ውዴ ሆይ፡ የግብጽን ንጉሥ ሠረገሎች ከሚስቡ ፈረሶች መካከል እንደ አንዲቱ ባዝራ ውብ ነሽ። 10 ጉንጮችሽ በጉትቻ አንገትሽም በዕንቁ ሐብል አጊጠዋል። 11 እኔም ባለ ብር ፈርጥ የወርቅ ጉትቻ አሠራልሻለሁ። ሙሽራዪቱ 12 ንጉሡ በድንክ አልጋው ላይ አረፍ ብሎ ሳለ፥ የሽቶዬ መዓዛ ክፍሉን ሁሉ ሞላው። 13 ውዴ ልክ በአንገቴ ላይ እንደታሰረ የተቋጠረ ከርቤ ሲመሽ በጡቶቼ መካከል ያርፋል። 14 ውዴ ለእኔ ከዓይንጋዲ የወይን ተክል ቦታ የመጣ የአበባ እቅፍ ነው። ሙሽራው 15 15. ውዴ ሆይ ውብ ነሽ፡ ቁንጅናሽም እጅግ ያማረ ነው። ዓይኖችሽ እንደ ርግብ ደስ የሚሉ ናቸው። ሙሽራዪቱ 16 አንተ ውዴ ሆይ፡ እጅግ ውብ ነህ፡በጣምም ታምራለህ። በገጠር ያለው ይህ ለምለም ሣር እንደምንተኛበት አልጋ ደስ የሚል ነው። 17 የዝግባ ቅርንጫፎች ይከልሉናል፡ከላይ ያሉትም ቅርንጫፎች ልክ እንደ ጣሪያ ይሆኑልናል።