1 ይህ መጽሐፍ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኔ ለዮሐንስ ያሳያቸው ነገሮችን ይዞአል። እግዚአብሔር እነዚህ ነገሮችን ለኢየሱስ ያሳየው፣ እርሱ ለአገልጋዮቹ እንዲያስተላልፍ ነው። እነዚህ ነገሮች ቶሎ የሚፈጸሙ ናቸው። ለእኔ ለአገልጋዩ እነዚህን ነገሮች እንዲያስተላልፍ ኢየሱስ መልአኩን ላከ። 2 እንደ አንድ አገልጋይ እኔ ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር ቃል ያየሁትንና የሰማሁትን፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጡ እውነተኛ ታሪኮችን ሁሉ ጽፌአለሁ። 3 ለሚሰማ ሁሉ እነዚህን ቃሎች ለሚያነብ ሰው እግዚአብሔር መልካም ያደርጋል። እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙበት ጊዜ በጣም እየቀረበ በመምጣቱ፣ በጥንቃቄ ለሚያደምጧቸውና ለሚታዘዟቸው ሁሉ እግዚአብሔር መልካም ነገር ያደርጋል። 4 እኔ ዮሐንስ ይህን መልእክት በእስያ አውራጃ ላሉ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት እጽፋለሁ። እግዚአብሔር ቸር ይሁንላችሁ፤ ሰላሙንም ይስጣችሁ፣ ምክንያቱም እርሱ ሁሌም የነበረ፣ አሁን ያለና ወደ ፊትም ለዘላለም የሚኖር ነው። በዙፋኑ ፊት የሚቀመጡ ሰባቱ መናፍስት እንዲሁ ያድርጉላችሁ። 5 እግዚአብሔርን በተመለከተ በታማኝነት እውነቱን የነገረን ኢየሱስ ክርስቶስም ቸር ይሁንላችሁ፤ ሰላምንም ይስጣችሁ። እርሱ እግዚአብሔር በመጀምሪያ ከሙታን ያስነሣው ነው፤ በምድር ነገሥታትም ላይ የሚፈርድ እርሱ ነው። መስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የወደደንና ኃጢአት ካስከተለው በደለኝነት በደሙ ነጻ ያወጣን እርሱ ነው። 6 በመንግሥቱ የሚገዛ እርሱ ነው፤ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡና እርሱ እንዳዘዘው ለአባቱ የሚሰግዱካህናት እንድንሆን የለየን እርሱ ነው። ለዘላለም ማክበርና ማመስገን የሚገባን ኢየሱስ ክርስቶን ነው። እውነቱ ይኸው ነው። 7 እነሆ ክርስቶስ በደመና ይመጣል። መስቀል ላይ ቸንክረው የገደሉት እንኳ ሳይቀሩ ሰዎች ሁሉ ያዩታል። ማንኛውም ነገድ፣ ምድር ላይ የሚኖር ማንኛውም ሰው እርሱ ሲመጣ ሲያዩ በጣም ያዝናሉ፤ ያለቅሳሉ። እውነቱ ይኸው ነው! 8 ጌታ አምላክ እንዲህ ይላል፤ “እኔ ነገሮችን ሁሉ የጀመርኩ አልፋ ነኝ፤ እኔ ነገሮች ሁሉ እንዲያበቁ የማደርግ ዖሜጋ ነኝ። እኔ የነበርኩ፣ ያለሁና ሁሌም የምኖር ነኝ። በማንኛውም ነገርና በሁሉም ላይ የምገዛ እኔ ነኝ።” 9 አማኝ ወገናችሁ እኔ ዮሐንስ፣ ኢየሱስ እኛ ላይ ገዢ በመሆኑ፣ እኔም እንደ እናንተ መከራ እየተቀበልሁ ነው። ለእምነታችን መከራ የመቀበልን ጥሪ እንጋራለን። እርሱ ነገሮችን ሁሉ እንደሚገዛ እኛንም ይገዛል፤ የሚመጣውን ማንኛውንም መከራና ፈተና በትዕግሥት እንቀበላለን። ስለ እግዚአብሔር መልእክትና፣ ኢየሱስን በተመለከተም ለሰዎች እውነቱን በመናገሬ ታስሬ ፍጥሞ ወደምትባል ደሴት ተወሰድሁ። 10 ከሌሎች አማኞች ጋር ጌታን በምናመልክበት በአንዱ ቀን፣ በእግዚአብሔር መንፈስ ነበርሁ። ከኋላዬ የሚናገር ድምፅ ሰማሁ። ድምፁ የመለከት ዓይነት ድምፅ ነበር። 11 እንዲህም አለኝ፤ “የምታየውን ሁሉ በመጽሐፍ ጻፍና ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም በኤፌሶን፣ በሰምርኔስ፣ በጴርጋሞን፣ በትያጥሮን፣ በሰርዴስ፣ በፊላደልፍያና በሎዶቅያ ከተሞች ወዳሉት አማኞች ላከው። 12 እነዚህን ቃሎች ስሰማ፣ የሚናገረው ማን እንደሆነ ለማየት ዘወር አልሁ። ያኔ ሰባት የወርቅ መቅረዞች አየሁ። 13 በመቅረዞቹ መከከል ሰው የሚመስል አንድ ፍጡር ነበር (አልፎ አልፎም የሰው ልጅ በመባል ይጠራል)። እስከ እግሩ የሚደርስ ልብስ ለብሶ ነበር፤ ደረቱን በወርቅ መታጠቂያ ታጥቆ ነበር። 14 የራሱ ጠጉር እንደ ነጭ የበግ ጠጉር፣ አሁን ገና እንደ ወረደ በረዶ ነጭ ነበር። ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ። 15 እግሮቹ በእሳት እንደ ጋለ ናስ ፍም ይመስሉ ነበር። ሲናገር፣ ድምፁ እንድ ታላቅ ወንዝ ወራጅ ውሃ ነበር። 16 በቀኝ እጁ ሰባት ከዋክብት ነበሩ። በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ከአፉ ይወጣ ነበር። ፊቱ በሙሉ ድምቀት እንደሚያበራ ፀሐይ ነበር። 17 ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ እግሩ ሥር ወደቅሁ። ሆኖም፣ ቀኝ እጁን እኔ ላይ አድርጎ እንዲህ አለኝ፤ “አትፍራ! ነገሮችን ሁሉ የጀመርሁ እኔ ነኝ፤ ነገሮች ሁሉ እንዲያበቁ የማደርግም እኔ ነኝ። 18 ሞቼ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ሕያው ነኝ፤ እንዲያውም ለዘላለሙ ሕያው ነኝ! ሞት ላይ ሥልጣን አለኝ፤ ሲኦልንም እቆጣጠራለሁ። 19 ስለዚህ ያየኸውን ጻፍ። አሁን እየሆነ ያለውን ጻፍ። ወደ ፊት የሚሆነውንም ጻፍ። 20 በቀኝ እጄ ያየሃቸው ሰባት ከዋክብትና የሰባቱ ወርቅ መቅርዞች ትርጕም ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት በእስያ ያሉ ሰባት አብያተ ክርስቲያናትን የሚጠብቁ መላእክት ይወክላሉ፤ ሰባቱ መቅረዞችም በዚያ ያሉ ሰባት አብያተ ክርስቲያናትን ሁሉ ይወክላሉ።”