1 የእስራኤል ንጉስ፣ የዳዊት ልጅ የሰለሞን ምሳሌዎች፡፡ 2 እነዚህ ምሳሌዎች የተጻፉት ጥበብንና ተግሳጽን፣ አርቆ ለማስተዋል የሚያስችሉ ቃላትን፣ 3 እርማትን በመቀበል ጽድቅ፣ ፍትሕና ሚዛናዊ የሆነ ብያኔን በማድረግ እንድትኖር ለማስተማር ነው፡፡ 4 ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ምሳሌዎች የተጻፉት ላልተማሩ ጥበብን፣ ለወጣቶች ደግሞ እውቀትንና ልባምነትን ለመስጠት ነው፡፡ 5 ጥበበኞች ያድምጡና ትምህርታቸውን ያዳብሩ፣ አስተዋዮች ደግሞ ምሪትን ያግኙበት፣ 6 ይህ ደግሞ የጠቢባንን ምሳሌዎች፣ አባባሎችና ቃላቶች እንደዚሁም እንቆቅልሾቻቸውን እንዲረዱ ነው፡፡ 7 እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመርያ ነው፣ ሞኞች ግን ጥበብንና ተግሳጽን ይንቃሉ፡፡ 8 ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው፤ 9 ለራስህ የሞገስ አክሊል፣ ለአንገትህ ደግሞ ውበት የሚሰጥ ጌጥ ይሆኑልሃል፡፡ 10 ልጄ ሆይ፣ ኃጢአተኞች በኃጢአታቸው እንድትሳተፍ ሊያባብሉህ ቢሞክሩ፣ እሺ አትበላቸው፡፡ 11 “ከእኛ ጋር ና፣ ነፍስ ለመግደል ተደብቀን እንጠብቅ፣ ንጹሐን ሰዎችን ያለ ምንም ምክንያት ለማትፋት እንሸምቅበት፡፡ 12 ሲኦል ጤናማ ሰዎችን እንደሚውጣቸው፣ ወደ ጉድጓድ እንደሚወርዱ፣ እንዲሁ በሕይወት እያሉ እንዋጣቸው፡፡ 13 ሁሉም አይነት ውድ የሆኑ ነገሮች እናገኛለን፤ ከሌሎች ሰዎች በሰረቅናቸው ነገሮች ቤቶቻችንን እንሞላለን፡፡ 14 ከእኛ ጋር ዕጣህን ጣል፤ ሁላችንም አንድ የጋራ ቦርሳ ይኖረናል፡፡” ቢሉህ፣ 15 ልጄ ሆይ፣ ከእነርሱ ጋር በዚያ መንገድ አትሂድ፤ እነርሱ በሚሄዱበት መንገድ እግርህ አይርገጥ፤ 16 እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉ፣ ደም ለማፍሰስም ይቸኩላሉ፡፡ 17 ወፍ ፊት ለፊት እያየች ወፍን ለመያዝ ወጥመድ መዘርጋት ጥቅም የለውም፡፡ 18 እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ለመግደል ተደብቀው ይጠብቃሉ፣ በራሳቸው ላይ ወጥመድን ይዘረጋሉ፡፡ 19 ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ሀብትን ያከማቹ ሰዎች መንገዳቸው እንደዚህ ነው፣ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የተከማቸ ሃብት የባለቤቱን ሕይወት ያጠፋል፡፡ 20 ጥበብ በጎዳና ላይ ጮኻ ትጣራለች፣ በአደባባይም ድምጿን ከፍ ታደርጋለች፤ 21 ጩኸት በበዛባቸው ጎዳናዎች ላይ ትጣራለች፣ በከተማ መግቢያ በሮች ላይ እንዲህ በማለት ትናገራለች፣ 22 እናንተ ጥበብ የሌላችሁ አላዋቂነትን የምትወዱት እስከ መቼ ነው? እናንተ ፌዘኞች በፌዝ የምትደሰቱት እስከ መቼ ነው? እናንተ ሞኞች እውቀትን የምትጠሉት እስከ መቼ ነው? 23 ለዘለፋየ ትኩረት ስጡ፤ ሃሳቤን ሁሉ ለእናንተ አፈስሳለሁ፤ ቃሎቼን አሳውቃችኋለሁ፡፡ 24 ጠራኋችሁ፣ እናንተ ግን ለመስማት እምቢ አላችሁ፤ እጄን ለእናንተ ዘረጋሁ፣ ነገር ግን አንድም ሰው ትኩረት አልሰጠውም፡፡ 25 ነገር ግን እናንተ ተግሳጼን በሙሉ ችላ አላችሁ፣ ለዘለፋየ ደግሞ ትኩረት አልሰጣችሁም፡፡ 26 እኔ ደግሞ በመከራችሁ እስቃለሁ፣ ሽብር በመጣባችሁ ጊዜ አላግጥባችኋለሁ፣ 27 አስፈሪ ድንጋጤ እንደ ማዕበል በእናንተ ላይ ሲመጣባችሁ፣ ጥፋት እንደ አውሎ ነፋስ እናንተን ሲጠራርጋችሁ፣ ጭንቅና ችግር በእናንተ ላይ በመጣ ጊዜ፡፡ 28 በዚያን ጊዜ ይጠሩኛል፣ እኔም አልመልስላቸውም፤ አጥብቀው ይፈልጉኛል፣ ነገር ግን አያገኙኝም፡፡ 29 እውቀትን ስለ ጠሉ፣ እግዚአብሔርን መፍራት ስላልመረጡ፣ 30 ምክሬን አልተከተሉምና፣ ዘለፋየንም ሁሉ ናቁ፡፡ 31 የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ፣ በእቅዳቸው ፍሬ ይጠግባሉ፡፡ 32 እነዚህ ያልተማሩ ሰዎች ከእውቀት መራቃቸው ይገድላቸዋል፣ ሞኞችንም ቸልተኝነታቸው ያጠፋቸዋል፡፡ 33 ነገር ግን የሚያደምጠኝ ሁሉ በሰላም ይኖራል፣ ከመከራም ስጋት ያርፋል፡፡