1 ያህዌ ከመገናኛው ድንኳን ሆኖ ሙሴን ጠርቶ እንዲህ አለው፣ 2 “ለእስራኤላዊያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፣ ‘ከእናንተ መሃል ማንም ሰው ለያህዌ መባ በሚያቀርብበት ጊዜ ከከብቶቻችሁ ወይም ከመንጋው እንስሳት መሃል አንዱን ያቅርብ፡፡ 3 መባው ከመንጋው መሃል የሚቃጠል መስዋዕት ከሆነ፣ ነውር የሌለበት ወንድ መስዋዕት ያቅርብ፡፡ መስዋዕቱ በያህዌ ፊት ተቀባይነት ያለው ይሆን ዘንድ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ያቅርበው፡፡ 4 በሚቃጠለው መስዋዕት ራስ ላይ እጁን ይጭናል፣ ይህም በእርሱ ምነትክ ያስተሰርይለት ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል፡፡ 5 ከዚያ በያህዌ ፊት ወይፈኑን ይረድ፡፡ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ካህናቱ የአሮን ልጆች ደሙን ያቀርቡና በመሰዊያው ላይ ይረጩታል፡፡ 6 ከዚያም ካህኑ የመስዋዕቱን ከብት ቆዳ መግፈፍና ብልቶችንም ማውጣት ይኖርበታል፡፡ 7 ከዚያም ካህናቱ የአሮን ልጆች በመሰዊያው ላይ ዕሳት ይለኩሱና እንጨት ይጨምሩበታል፡፡ 8 ካህናቱ የአሮን ልጆች የስጋውን ብልቶች፣ የከብቱን ጭንቅላትና ስቡን በመስዋዕቱ ምድጃ ላይ በሚገኘው እንጨት ላይ በስርዓት ይደረድሩታል፡፡ 9 ነገር ግን ካህኑ የመስዋዕቱን ሆድቃና እግሮቹን በውሃ ማጠብ ይኖርበታል፡፡ በመስዋዕቱ ላይ የሚገኘውን ሁሉ የሚቃጠል መስዋዕት አብርጎ ያቃጥለዋል፡፡ ይህም ለእኔ ጣፋጭ ሽታ ይሆናል፤ ይህም ለእኔ በዕሳት የቀረበ መስዋዕት ይሆናል፡፡ 10 ለመስዋዕት የሚያቀርበው የሚቃጠል መስዋዕት ከመንጋው ከሆነ፣ ከበጎች ወይም ከፍየሎች መሃል ነውር የሌለበት ተባዕት መስዋዕት ማቅረብ አለበት፡፡ 11 በያህዌ ፊት መስዋዕቱን ከመሰዊያው በስተቀኝ በኩል ይረደው፡፡ ካህናቱ የአሮን ልጆች የመስዋዕቱን ከብት ደም በመሰዊያው ዙሪያ ሁሉ ይርጩት፡፡ 12 ከዚያ ካህኑ የመስዋዕቱን ከብት ጭንቅላቱንና ስቡን እንዲሁም ብልቶቹን ይቆራርጥ፡፡ ከዚያም በመሰዊያው በሚገኘው የሚነድ እንጨት ላይ በስርዓት ይደርድረው፡፡ 13 ነገር ግን የመስዋዕቱን ሆድቃና እግሮቹን በውሃ ይጠብ፡፡ ከዚያ ካህኑ መባውን በሙሉ ያቅርብና በመሰዊያው ላይ ያቃጥለው፡፡ ይህም የሚቃጠል መስዋዕት ነው፣ ለያህዌ ጣፋጭ መዓዛ ይሆናል፤ ለእርሱ በዕሳት የተዘጋጀ መስዋዕት ይሆናል፡፡ 14 “ካህኑ ለያህዌ የሚያቀርበው የሚቃጠል የወፎች መስዋዕት ከሆነ፣አንድ ወፍ ወይም ዕርግብ ማቅረብ አለበት፡፡ 15 ካህኑ መስዋዕቱን ወደ መሰዊያው ያመጣና አንገቱን ይቆለምመዋል፣ ከዚያም በመሰዊያው ላይ ያቃጥለዋል፡፡ ደሙም በመሰዊያው ጎን ተንጠፍጥፎ ይፈሳል፡፡ 16 የወፉን ማንቁርትና በውስጡ ያሉትን ያስወግድ፣ ከዚያም አመድ በሚደፉበት ከመሰዊያው በስተ ምስራቅ ይወርውረው፡፡ 17 ክንፎቹን ይዞ ይሰንጥቀው፣ ነገር ግን ለሁለት አይክፈለው፡፡ ከዚያ ካህኑ በዕሳቱ ላይ ባለው እንጨት መሰዊያው ላይ ያቃጥለው፡፡ ይህ የሚቃጠል መስዋዕት ይሆናል፣ እናም ለያህዌ ጣፋጭ ማዕዛ ይሆናል፣ ይህ ለእርሱ በዕሳት የተዘጋጀ መስዋዕት ይሆናል፡፡”