ምዕራፍ 1

1 ዖጽ በሚባል ምድር ኢዮብ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ኢዮብም በደል የማይገኝበት፤ ትክክለኛ፤ እግዚአብሄርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው ነበረ። 2 ለእርሱም ሰባት ወንዶችና ሶስት ሴቶች ልጆች ተወልደውለት ነበር። 3 ሰባት ሺህ በጎች፤ ሶስት ሺህ ግመሎች፤ አምስት ሺህ ጥንድ በሬዎችና አምስት ሺህ አህዮች እንዲሁም እጅግ ብዙ ሰራተኞች ነበሩት። ይህም ሰው በምስራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ሰው ነበር። 4 ወንዶች ልጆቹም በየተመደበላቸው ተራ በያንዳንዳቸው ቤት ግብዣ ያደርጉ ነበር፤ ሦስቱ እኅቶቻቸውም ከእነርሱ ጋር እንዲበሉና እንዲጠጡ ልከው ይጠሩአቸው ነበር። 5 የግብዣቸውም ቀናቶች ሲያበቁ ኢዮብ፦ ያስጠራቸውና ለእግዚአብሔር መልሶ ይቀድሳቸው ነበር።ማልዶ በጠዋት ተነስቶ “ምናልባት ልጆቼ በድለው፥ እግዚአብሔርንም በልባቸው ረግመው ይሆናል” ብሎ ፤ ለልጆቹ ለእያንዳንዳቸው የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል። ይህንንም ኢዮብ ሁልጊዜ ያደርግ ነበር። 6 በኋላም የእግዚአብሔር ልጆች በያህዌ ፊት ራሳቸውን የሚያቀርቡበት ቀን ነበረ ፥ ሰይጣንም ደግሞ ከእነርሱ ጋር መጣ። 7 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦“ ከወዴት እየመጣህ ነው?” አለው። ሰይጣንም ለእግዚአብሔር ሲመልስ፦ “ምድርን ሁሉ ዞርሁ፥ በእርስዋም ላይ ወዲህና ወዲያ ተመላልሼ መጣሁ” አለ። 8 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ”በውኑ ባሪያዬን ኢዮብንስ ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ያለ በደል የማይገኝበት ትክክለኛ ሰው ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም“ አለው። 9 ሰይጣንም ለእግዚአብሔር ሲመልስ እንዲህ አለ፦ “ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራው እንዲሁ ነውን? 10 በእርሱና በቤቱ ባለውም ነገር ሁሉ ዙሪያ በየአቅጣጫው አጥር አላደረግህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፥ ሐብቱም በምድር ላይ በዝቶአል። 11 ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሀብት ሁሉ አውድም ፤ ፊትለፊት ይክድሃል።” 12 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ “እነሆ እርሱ ያለው ነገር ሁሉ በስልጣንህ ስር ነው፥ በእርሱ ላይ ግን ጉዳት እንዳታደርስ” አለው። ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄደ። 13 ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ በታላቅ ወንድማቸው ቤት በሚበሉበትና የወይን ጠጅ በሚጠጡበት ቀን እንዲህ ሆነ፤ 14 መልክተኛ ወደ ኢዮብ መጥቶ፦ ”በሬዎች እርሻ እያረሱ፥ በአጠገባቸውም አህዮች ተሰማርተው ነበር፤ 15 የሳባም ሰዎች አደጋ አድርሰው ወሰዱአቸው፥ ሰራተኞቹንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እኔም እንድነግርህ ብቻዬን አመለጥሁ“ አለው። 16 እርሱም ገና እየተናገረ ሳለ ሌላ መጥቶ፦“ የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወደቀ፥ በጎቹንና ጠባቂዎችን አቃጥሎ በላቸው፤ እኔም እንድነግርህ ብቻዬን አመለጥሁ“ አለው። 17 እርሱም ገና እየተናገረ ሳለ ሌላ መጥቶ፦ ”ከለዳውያን በሦስት ቡድን ተከፍለው በግመሎች ላይ አደጋ ጥለው ወሰዱአቸው ፥ ሰራተኞቹንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እኔም እንድነግርህ ብቻዬን አመለጥሁ“ አለው። 18 እርሱም ገና እየተናገረ ሳለ ሌላ መጥቶ፦ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት እየበሉና የወይን ጠጅ እየጠጡ ነበር፤ 19 ታላቅ ነፋስ ከምድረ በዳ መጥቶ የቤቱን አራቱን ማዕዘን መታውና በልጆቹ ላይ ወደቀ፥ እነርሱም ሞቱ፤ እኔም እንድነግርህ ብቻዬን አመለጥሁ“ አለው። 20 ኢዮብም ተነሣ ልብሱንም ቀደደ፥ ራሱንም ተላጨ፥ በምድርም ላይ በፊቱ ተደፍቶ እግዚአብሔርን አመለከ፤ 21 እንዲህም አለ፦ ”ከእናቴ ማኅፀን ራቁቴን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ወሰደ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን።“ 22 በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ኢዮብ ሐጢያት አላደረገም፥ በስንፍናም እግዚአብሔርን አልከሰሰም።