ምዕራፍ 1

1 በመጀመሪያ ቃል ነበር፡፡ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሔር ነበር፡፡ 2 አንዳች ነገር መፍጠር ከመጀመሩ አስቀድሞ እርሱ ከእግዚአብሔር ጋር ነበር፡፡ 3 ሁሉንም ነገር ለመፍጠር የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ያከናወነው እርሱ ነው፡፡ አዎን፣ የተሰራው ነገር ፍጹም አንዳች ሳይቀር የሰራው በእርሱ ነው! 4 ህይወት ሁሉ በቃል ውስጥ ነው፣ ስለዚህ እርሱ ለሁሉም ነገር እና ለእያንዳንዱ ህይወት መስጠት ይችላል፡፡ ቃሉ በእያንዳንዱ ላይና በሁሉም ስፍራ የሚያበራ የእግዚአብሔር ብርሃን ነበር፡፡ 5 ይህ ብርሃን በጨለማ ሲያበራ ጨለማው ሊያስወግደው ሞከረ ነገር ግን አልቻለም፡፡ 6 እግዚአብሔር ስሙ ዮሐንስ የተባለ ሰው ላከ፡፡ 7 እርሱ ስለ ብርሃን ለሰዎች ሊመሰክር መጣ፡፡ የተናገረው እውነት ነበር፣ እያንዳንዱ ያምን ዘንድ እርሱ ያንን መልዕክት አወጀ፡፡ 8 ዮሐንስ ራሱ ያን ብርሃን አልነበረም፣ ነገር ግን ስለዚያ ብርሃን ለሰዎች ለመናገር መጣ፡፡ 9 በእያንዳንዱ ላይ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ይህ ነበር፣ እናም ያብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር፡፡ 10 ቃል በዓለም ውስጥ ነበር፣ እርሱ ዓለምን ቢሰራም እንኳን፣ እርሱ ማን እንደነበር ከዓለም ህዝብ ማንም አላወቀም፡፡ 11 የእርሱ ወደ ሆነ ዓለምና፣ ወደ ራሱ ሰዎች ወደ አይሁዶች ቢመጣም እንኳን አልተቀበሉትም፡፡ 12 ነገር ግን እርሱን ወደ ህይወታቸው በተቀበሉና በእርሱ ላመኑ ሁሉ፣ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት ሰጣቸው፡፡ 13 እነዚህ ከእግዚአብሔር የተወለዱ ልጆች ናቸው፡፡ በተለመደው የሰው አወላለድ ወይም ከሰው ፍላጎት ወይም ምርጫ በመነሳት ወይም ከባል አባት የመሆን ፍላጎት ምክንያት የተወለዱ አይደሉም፡፡ 14 አሁን ቃል ተጨባጭ ሰው ሆኖ እኛ ለጊዜው በምንኖርበት በዚህ ኖረ፡፡ እግዚአብሔር እኛን በታማኝነት መወደዱንና ስለ እርሱ እውነት ያስተማረንን አንድና ብቸኛ የአብ ልጅ ባህሪ የሆነውን ድንቅና አስገራሚ ባህሪውን ሲገልጽ አየነው፡፡ 15 አንድ ቀን አጥማቂው ዮሐንስ ስለ ቃል ለሰዎች ይናገር ነበር፣ በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ወደ እርሱ መጣ፡፡ ዮሐንስ በዙሪያው ለነበሩ ሰዎች ጮህ ብሎ እንዲህ በማለት ተናገረ፣ “ከእኔ በኋላ ከእኔ ይልቅ እጅግ ጠቃሚ የሆነ አንድ ሰው ይመጣል በማለት ነግሬያችሁ ነበር፡፡ ከእኔ እጅግ አስቀድሞ ነበረ፣ በዘላለም ዘመናት፣ እኔ ከመወለዴ አስቀድሞ ነበረ፡፡ ይህ ሰው እነሆ በዚህ! ስለ እርሱ ስናገርለት የነበረው ሰው ይህ ነው!” 16 እኛ ሁላችንም እርሱ ከሰራው ብዙ ተጠቅመናል፡፡ እርሱ ደግሞ ደጋግሞ በጣም በደግነት ለእኛ ሰርቷልና፡፡ 17 ሙሴ የእግዚአብሔርን ህጎች ለአይሁድ ህዝብ አውጇል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እግዚአብሔር እውነቱን በቸርነት አስተምሮናል፡፡ 18 ማንም እግዚአብሔርን አይቶት አያውቅም፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር አንዲያ ልጅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለጊዜ ለአብ ቅርብ የሆነው እርሱ እግዚአብሔርን እንድናውቀው አድርጓል፡፡ 19 ዮሐንስ የሰጠው ምስክርነት ይህ ነው፡፡ አይሁዶች ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋዊያንን ላኩ፤ ዮሐንስን “አንተ ማን ነህ?” ብለው ለመጠየቅ መጡ፡፡ 20 ስለዚህም ዮሐንስ ለእነርሱ ምስክርነቱን እንዲህ ሲል ሰጠ፣ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም!” 21 ከዚያ እነርሱ እንዲህ ብለው ጠየቁት፣ “ስለ ራስህ ምን ትላለህ? ኤሊያስ ነህን?” እርሱ “አይደለሁም” አለ፡፡ እነርሱ እንደገና ጠየቁት፣ “ነቢያት ይመጣል ያሉት ነቢዩ ነህ?” ዮሐንስ፣ “አይደለም” ሲል መለሰ፡፡ 22 ስለዚህ አንድ ጊዜ በተጨማሪ ጠየቁት፣ “ታዲያ ማን ነኝ ትላለህ? ወደ ላኩን ተመልሰን ሄደን መመለስ እንድንችል ንገረን፡፡ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” 23 እርሱ እንዲህ ሲል መለሰ፣ “ነቢዩ ኢሳይያስ ‘ወደ እኛ እንዲመጣ ለጌታ መንገዱን አቅኑ፡፡’ ሲል እንደጻፈው እኔ በበረሃ የሚጮኸው ነኝ፡፡” 24 ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ ከፈሪሳውያን ዘንድ ወደ ዮሐንስ መጡ፡፡ 25 እንዲህ ብለውም ጠየቁት፣ “አንተ ክርስቶስ ወይም ኤሊያስን ወይም ነቢዩን አለመሆንህን እስከተናገርክ ድረስ ታዲያ ለምን ታጠምቃለህ?” 26 ዮሐንስ እንዲህ ሲል መለሰ፣ “እኔ ሰዎችን በውሃ አጠምቃለሁ፣ ነገር ግን አሁን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ የቆመ አንድ ሰው አለ፡፡ 27 እርሱ ከእኔ በኋላ ይመጣል፣ ነገር ግን እኔ የእርሱን የጫማ መሳሪያዎች ለመፍታት የምበቃ አይደለሁም፡፡ 28 እነዚህ ነገሮች የሆኑት ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምስራቅ በኩል በቢታኒያ መንደር ነው፡፡ ዮሐንስ ያጠምቅ የነበረው በዚያ ስፍራ ነው፡፡ 29 ዮሐንስ በማግስቱ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አየ፡፡ እርሱም ለህዝቡ እንዲህ አለ “ተመልከቱ! የዓለምን ሀጢአት ለማስወገድ የራሱን ህይወት መስዋዕት አድርጎ የሚሰጥ የእግዚአብሔር በግ፡፡ 30 ‘ከእኔ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ከእኔ በኋላ የሚመጣ፣ ምክንያቱም ከእኔ በፊት እጅግ ቀድሞ የነበረ፣ ዘላለማዊ፣ እኔ ከመወለዴ በፊት የነበረ ነው፡፡’ ያልኩት እርሱ ነው፡፡ 31 በመጀመሪያ አላውቀውም ነበር፣ ነገር ግን አሁን እርሱ ማን እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ የእኔ ስራ የተፀፀቱትንና ከሀጢአታቸው የተመለሱትን መጥቼ በውሃ ማጥመቅ ነበር፡፡ እኔ እርሱ ማን እንደሆነ የእስራኤል ሰዎች እንዲያውቁ እፈልጋለሁ፡፡ 32 ምን እንደተመለከተ ለእኛ መናገር ይህ የዮሐንስ ሥራ ነበር፡፡ እሱ እንዲህ ተናገረ፣ “የእግዚአብሔር መንፈስ በእርግብ መልክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፡፡ መንፈሱ ወደ ታች መጥቶ በኢየሱስ ላይ ኖረ፡፡ 33 በመጀመሪያ እኔ ራሴ አላወኩትም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ከሀጢአተኝነት መንገዳቸው መመለስ እንፈልጋለን የሚሉ ሰዎችን በውሃ እንዳጠምቅ ላከኝ፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ነገረኝ፣ ‘መንፈሴ ሲወርድበትና በእርሱ ላይ ሲኖርበት የምታይበት ሰው እርሱ ሁላችሁንም በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው ይሆናል፡፡’ 34 እኔ አይቻለሁ እሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለእናንተ በእርግጠኝነት እመሰክራለሁ፡፡” 35 አጥማቂው ዮሐንስ በቀጣዩ ቀን እንደገና ከሁለቱ ደቀመዛሙርቱ ጋር በተመሳሳይ ቦታ ነበር፡፡ 36 ኢየሱስ ሲያልፍ ተመልክቶ እንዲህ አለ፣ “ተመልከቱ! እነሆ የእግዚአብሔር በግ፣ እግዚአብሔር የእሱን ሕይወት አሳልፎ እንዲሰጥ የላከው ሰው፣ በእስራኤላውያን ሰዎች ስለ ሀጢአታቸው ክፍያ እንደ ጠቦት ይታረዳል! 37 ሁለቱ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት፣ ዮሐንስን በሰሙት ጊዜ፣ ዮሐንስን ትተው እርሱን ተከተሉት፤ 38 ኢየሱስ ወደ ኋላ ዞር አለና እርሱን ሲከተሉት አያቸው፣ እናም እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፣ “ምን እየተመለከታችሁ ነው?’ እነርሱም እንዲህ አሉት፣ “ረቢ (‘መምህር’ ማለት ነው) የት እንደምትኖር ንገረን?” 39 እርሱ ሲመልስ፣ “ከእኔ ጋር ኑና ታያላችሁ!” አላቸው፡፡ ስለዚህም መጥተው ኢየሱስ የት እንደሚኖር አዩ፣ እናም በዚያ ቀን ከእርሱ ጋር ቆዩ፣ እየመሸ ነበር፡፡ (ከረፋዱ 10 ሰዓት ነበር፡፡) 40 ከተከተሉት ሁለት ደቀመዛሙርት የአንዱ ስም እንድርያስ ነበር፤ እርሱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም ነበር፡፡ 41 በመጀመሪያ እንድርያስ ወንድሙን ስምዖንን ሊፈልግ ሄደ፡፡ ሲያገኘው እንዲህ አለ፣ “መሲሁን (‘ክርስቶስ’ ማለት ነው) አገኘነው!” 42 እንድርያስ ስምዖንን ወደ ኢየሱስ ወሰደው፡፡ ኢየሱስ በጉጉት ዐይን ወደ ጴጥሮስ እየተመለከተ እንዲህ አለ፣ “አንተ ስምዖን ነህ፡፡ የአባትህ ስም ዮሐንስ ነው፡፡ ኬፋ የሚባል ስም ይሰጥሃል፡፡” ኬፋ የአረማይክ ስም ነው፡፡ ትርጉሙም ‘ጠንካራ አለት’ ማለት ነው፡፡ (በግሪክ ጴጥሮስ ማለት ተመሳሳይ ትርጉም አለው፡፡) 43 በቀጣዩ ቀን ኢየሱስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝን ሸለቆ ለመሄድ ወሰነ፡፡ በገሊላ ዙሪያ ወደሚገኝ አካባቢ ሄደና ፊልጶስ የተባለ አንድ ሰው አገኘ፡፡ ኢየሱስ እርሱን እንዲህ አለው፣ “ከእኔ ጋር ና” 44 ፊሊጶስ፣ እንድርያስ እና ጴጥሮስ ሁሉም ከቤተሳይዳ (ገሊላ ውስጥ ትገኛለች) ከተማ ነበሩ፡፡ 45 ከዚያ ፊሊጶስ ጓደኛውን ናትናኤልን ለመፈለግ ሄደ፡፡ ወደ እርሱ ሲመጣ እንዲህ አለው “ሙሴ ስለ እርሱ የጻፈለትን፣ ክርስቶስን እኛ አግኝተነዋል፡፡ ነቢያት እርሱ እንደሚመጣ ተንብየዋል፡፡ የምንጠብቀው ክርስቶስ እርሱ ኢየሱስ ነው፡፡ እርሱ ከናዝሬት ከተማ ነው የአባቱ ስም ዮሴፍ ነው፡፡ 46 ናትናኤል እንዲህ ሲል መለሰ፣ “ከናዝሬት? ከናዝሬት መልካም ነገር ይገኛልን?” ፊሊጶስ እንዲህ ሲል መለሰ፣ “ና እና ታያለህ!” 47 ኢየሱስ ወደ እርሱ ናትናኤል ሲቃረብ አይቶ፣ እርሱን ከመገናኘቱ አስቀድሞ ናትናኤልን እንዲህ ሲል ገለጸው፣ “ቅን እና መልካም የሆነው እስራኤላዊ ይሄውና! እርሱ ፍፁም ማንንም አታሎ አያውቅም!” 48 ናትናኤል እንዲህ ሲል ጠየቀው፣ “እኔ ምን አይት ሰው እንደሆንኩ እንዴት ታውቃለህ? አንተ እኔን አታውቀኝም፡፡” ኢየሱስ፣ “ብቻህን ከበለስ ዛፍ ስር ተቀምጠህ ሳለህ፣ ፊሊጶስ አንተን ከመጥራቱ አስቀድሞ አየሁህ” ሲል መለሰለት፡፡ 49 ከዚያ ናትናኤል፣ “ረቢ፣ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን አለብህ! አንተ ስንጠብቅህ የቆየነው የእስራኤል ንጉስ ነህ!” በማለት ማመኑን በግልጽ ተናገረ፡፡ 50 ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰለት፣ “ከበለስ ዛፍ ስር አየሁህ ስላልህ ብቻ በእኔ አመንክን? ከዚያ እጅግ የሚበልጥ ነገሮችን ስሰራ ታየኛለህ!” 51 ከዚያ ኢየሱስ እንዲህ አለው፣ “እኔ እውቱን እየነገርኩህ ነው፡ ከረጅም ዘመን በፊት አባትህ ያዕቆብ እንዳየው አይነት ራዕይ ታያለህ፤ አንድ ቀን ሰማይ ሲከፈት እናም የእግዚአብሔር መላዕክት በእኔ በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያለህ፡፡”