1 በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር እስረኛና አገልጋይ የሆነ ያዕቆብ በክርስቶስ ኢየሱስ ለሚያምኑና በመላው ዓለም ለተበተኑት ለአሥራ ሁለቱ ነገዶች ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡ 2 ወንድሞቼ ሆይ፣ በልዩ ልዩ ፈተናዎች ውስጥ ማለፋችሁን እጅግ ደስ እንደሚያሰኝ ነገር ቊጠሩት፡፡ 3 በፈተና ውስጥ ሳላችሁ በእግዚአብሔር ስታምኑ ይበልጥ ሌሎች ፈተናዎችን በትዕግሥት ለማሳለፍ የሚረዱዋችሁ መሆኑን ትረዳላችሁ፡፡ 4 ክርስቶስን በሁሉም መንገድ ትከተሉ ዘንድ እስከ መጨረሻው በፈተና ጽኑ፤ ያንጊዜ መልካም ማድረግ አይከብዳችሁም፡፡ 5 ከእናንተ አንዱ ምን ማድረግ እንዳለበት ማወቅ ከፈለገ፣ በሚጠይቀው ላይ ሳይቈጣ በልግሥና የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይጠይቅ፡፡ 6 እግዚአብሔርን ስትለምኑ፣ የምትጠይቁትን እንደሚሰጣችሁ እመኑ፤ መልስ እንደሚሰጣችሁና ሁልጊዜም እንደሚረዳችሁ አትጠራጠሩ፤ የሚጠራጠሩ ሰዎች እግዚአብሔርን ሊከተሉት አይችሉም፤ መጠራጠር ልክ ተመልሶ እንደሚመጣ፣ ደግሞም በዚያው አቅጣጫ መጓዝን እንደማይቀጥል የባሕር ማዕበል ያለ ነገር ነው፡፡ 7 በእርግጥ የሚጠራጠሩ ሰዎች የሚጠይቁትን ነገር ለመፈጸም እግዚአብሔር አንድ ነገር ሊያደርግ እንደሚችል አያምኑም፡፡ 8 እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለመከተል ወይም ላለመከተል ያልወሰኑ ናቸው፤ እነዚህም የሚናገሩትን ነገር የማያደርጉ ሰዎች ናቸው፡፡ 9 ድሀ የሆኑ አማኞች እግዚአብሔር ስላከበራቸው ደስ ሊሰኙ ይገባል፡፡ 10 ባለጠጋ የሆኑ አማኞችም እግዚአብሔር ትሑታን ስላደረጋቸው ደስ ሊሰኙ ይገባል፤ ልክ የበረሃ አበቦች እንደሚደርቁ ሁሉ፣ እነርሱም ሆኑ ሀብታቸው የሚያልፉ ናቸውና፡፡ 11 ፀሐይ በሚወጣ ጊዜ ሞቃታማ የሆነው ነፋስ ተክሎችን ያደርቃል፤ ደግሞም አበቦችን በምድር ላይ እንዲወድቁም ሆነ በውበታቸው እንዳይቀጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ባለ ጠጎች ልክ እንደሚሞቱ አበቦች ሁሉ ገንዘብን እየሰበሰቡ ሳሉ ይሞታሉ፡፡ 12 በመከራ የሚጸኑትን ሰዎች እግዚአብሔር ያከብራቸዋል፤ ለሚወድዱት ሁሉ ተስፋ እንደ ሰጠው ለዘላለም እንዲኖሩ በማድረግ ብድራታቸውን ይከፍላቸዋል፡፡ 13 በኃጢአት ስንፈተን እግዚአብሔር እየፈተነን ነው ብለን ልናስብ አይገባም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ክፉን እንድንሠራ አይፈልግምና፤ ክፉን እንዲያደርግ ማንንም አይፈትንምና፡፡ 14 ዳሩ ግን ሰዎች ሁሉ ክፉ ማድረግን ይፈልጋሉ፤ ስለዚህም በወጥመድ የተጠመዱ ይመስል ይህን ያደርጉታል፡፡ 15 ከዚያም በኋላ ክፉ አሳቦቻቸው ኃጢአትን ወደ ማድረጉ ይመሩዋቸዋል፡፡ ይህም ደግሞ እስኪያጠፋቸው ድረስ ኃጢአት አሳባቸውን ይቆጣጠራል፡፡ ከዚያም ክፉ ምኞቶች በአንድነት ሲመጡ ኃጢአት ይወለዳል፤ ይህም ኃጢአትን የሠራው ሰው ይቅር ሊባል የሚችለው በክርስቶስ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ኃጢአትም የመጨረሻ ውጤትዋን ስትሰጥ ሞት ይመጣል፡፡ ይህም የመንፈስም ሆነ የሥጋ ሞት ሲሆን፣ ኃጢአተኛው ከእግዚአብሔር ይለያል ማለት ነው፡፡ ከእንደዚህ ዐይነቱ የመጨረሻ ሞት ሊያድነን የሚችል ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ 16 የምወዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ራሳችሁን ማታለልን አቁሙ፡፡ 17 ዕውነተኛ የሆነ መልካምና ፍጹም ስጦታ በሰማይ ካለው ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይመጣል፡፡ ፍጡራን ነገሮች እንደሚለወጡ፣ ጥላዎችም ተገልጠው እንደሚጠፉ፣ እግዚአብሔር አይለወጥም፡፡ እግዚአብሔር ከቶ አይለወጥም፤ እንዲሁም ሁልጊዜም ቢሆን እርሱ መልካም ነው፡፡ 18 በዕውነተኛ መልእክቱ በምናምን ጊዜ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ሕይወትን ሊሰጠን ይወዳል፡፡ ስለዚህም አሁን ኢየሱስ ብቻ ሊሰጠው የሚችለውን ዕውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ለማግኘት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አማኞች ይሆናሉ፡፡ 19 የምወዳችሁ ወዳጆቼ ሆይ፥ ዕውነተኛ ለሆነው የእግዚአብሔር መልእክት ትኲረት ልትሰጡ ይገባል፡፡ የምታስቡትን ነገር ለመናገር አትቸኩሉ፤ ፈጥናችሁም አትቈጡ፡፡ 20 በምንቈጣበት ጊዜ እግዚአብሔር እንድናደርገው የሚሻውን ነገር ማድረግ አንችልም፡፡ 21 እንግዲህ ሁሉንም ዐይነት ክፉ ነገሮች አስወግዱ፤ በትሕትናም እግዚአብሔር በውስጣችሁ ያስቀመጠውን መልእክት ተቀበሉ፤ መልእክቱን የምትቀበሉ ከሆናችሁ እርሱ ሊያድናችሁ ይችላል፡፡ 22 እግዚአብሔር በቃሉ ያዘዘውን ነገር አድርጉ፡፡ የምታዳምጡ ብቻ አትሁኑ፤ የሚያደምጡትና የማይታዘዙት ሰዎች በተሳሳተ መልኩ እንደሚያድናቸው ያስባሉ፡፡ 23 አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሔር ቃል መልእክትን ይሰማሉ፤ ነገር ግን ቃሉ የሚላቸውን አያደርጉም፤ እነዚህ ሰዎች ፊቱን በመስታወት የሚያይ ሰውን ይመስላሉ፡፡ 24 ይህ ሰው ምንም እንኳ ራሱን ቢመለከትም ከመስታወቱ ይሄዳል፤ ወዲያውም ደግሞ ያየውን ነገር ይረሳዋል፡፡ 25 ሌሎች ሰዎች ግን ፍጹም የሆነውንና እግዚአብሔር ያዘዘውን በፈቃደኝነት እንዲያደርጉ ነፃ የሚያደርጋቸውን የእግዚአብሔርን ቃል መልእክት በሚገባ ይከታተላሉ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል መልእክት የሚፈልጉ፣ ዝምብለው የሚሰሙትና የሚረሱቱ ካልሆኑ፣ ዳሩ ግን እግዚአብሔር አድርጉ የሚላቸውን የሚያደርጉ ከሆኑ፣ እነዚህን ሰዎች ባደረጉት ነገር ምክንያት እግዚአብሔር ይባርካቸዋል፡፡ 26 አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔርን በትክክል እንደሚያመልኩ ያስባሉ፤ ይሁንና ክፉ ንግግሮችን መናገር ለምዶባቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን በትክክል የሚያመልኩ እንደ ሆኑ በማሰባቸው ተሳስተዋል፡፡ ዕውነቱ ግን እግዚአብሔርን በከንቱ ማምለካቸው ነው፡፡ 27 እግዚአብሔር እንድናደርጋቸው ከነገረን ነገሮች መካከል አንዱ በችግር የሚያልፉ ወላጅ-አልባ ልጆችንና ባልቴቶችን መርዳት ነው፡፡ ይህን የሚያደርጉ፣ እንዲሁም እግዚአብሔርን የማይታዘዙ ሰዎች የሚያደርጉትን የማያስቡም ሆኑ የማይፈጽሙ ሰዎችን እግዚአብሔር ይቀበላቸዋል፡፡