1 የይሁዳ ነገሥታት በሆኑት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው የአሞጽ ልጅ የኢሳይያስ ራእይ። 2 ሰማያት ስሙ፣ ምድርም አድምጪ፤ "ልጆችን ወለድሁ አሳደግሁም፣ እነርሱም አመጹብኝ።" ሲል እግዚአብሔር ተናግሮአልና። 3 በሬ የገዢውን፣ አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቀም፥ እስራኤል አልተገነዘበም" 4 ወዮላችሁ! ኃጢአተኛ ወገንና በደል የተሞላበት ሕዝብ፣ የክፉ አድራጊዎች ልጆች፣ ርኵሰትን የምታደርጉ ልጆች ሆይ! እግዚአብሔርን ትተዋል፣ የእስራኤልንም ቅዱስ አቃልለዋል ወደ ኋላቸውም እየሄዱ ተለይተዋል። 5 አሁን ድረስ ለምን ትቀሰፋላችሁ? አሁንም አሁንም ዓመፃ ለምን ትጨምራላችሁ? ራስ ሁሉ ለሕመም፣ ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል። 6 ከእግር መርገጫ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ያልታመመ የለውም፤ ቍስልና እበጥ፣ የሚደማ ቊስል ነው፤ አልፈረጠም፣ አልተጠገነም፣ በዘይትም አልለዘበም። 7 ምድራችሁ ባድማ ናት፤ ከተሞቻችሁ በእሳት ተቃጠሉ፤ እርሻችሁንም በፊታችሁ እንግዶች ይበሉታል፤ ባዕድ እንዳፈረሳት ምድር ባድማ ሆነች። 8 የጽዮንም ሴት ልጅ በወይን ቦታ እንዳለ ዳስ፣ በዱባ አትክልትም እንዳለ ጎጆ፣ እንደተከበበችም ከተማ ሆና ቀረች። 9 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ጥቂት ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፣ እንደ ሰዶም በሆንን፣ እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር። 10 እናንተ የሰዶም አለቆች ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፣ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ። 11 "የመሥዋዕታችሁ ብዙ ጋጋታ ለእኔ ምን ይጠቅመኛል?" ይላል እግዚአብሔር። "የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም። 12 በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ፣ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው? 13 ምናምንቴውን ቍርባን ጨምራችሁ አታምጡ፤ ዕጣን በእኔ ዘንድ አጸያፊ ነው፤ መባቻችሁንና ሰንበታችሁን በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድድም - እነዚህን የረከሱ ጉባዔዎች አልታገሥም። 14 መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ። 15 ስለዚህም እጃችሁን በጸሎት ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፣ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል። 16 ታጠቡ፣ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ መሆንን ተዉ፤ 17 መልካም ማድረግን ተማሩ፣ ፍርድን ፈልጉ፣ የተጨቆነውን እርዱ፣ አባት ለሌለው ፍረዱለት፣ ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ።" 18 "አሁን ኑና በአንድ ላይ እንዋቀስ" ይላል እግዚአብሔር፤ "ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን፣ እንደ በረዶ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ፣ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። 19 እሺ ብትሉ ብትታዘዙ፣ የምድርን በረከት ትበላላችሁ። 20 ነገር ግን እምቢ ብትሉ፣ ብታምፁም፣ ሰይፍ ይበላችኋል፣" የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና። 21 ፍርድ ሞልቶባት የነበረችው የታመነችይቱ ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ጽድቅ ሞልቶባት ነበር፣ አሁን ግን ገዳዮች ሞልተውባታል። 22 ብርሽ ወደ ዝገት ተለወጠ፣ የወይን ጠጅሽ ከውሃ ጋር ተደባለቀ። 23 አለቆችሽ አመጸኞችና የሌቦች ባልንጀሮች ሆኑ፤ ሁሉ ጉቦ ይወድዳሉ፣ ዋጋም ለማግኘትም ይሮጣሉ። ለድሀ አደጉ አይፈርዱም፣ የመበለቲቱም ሙግት ወደ እነርሱ አይደርስም። 24 ስለዚህ የእስራኤል ኃያል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ወዮላቸው! የሚቋቋሙኝ ላይ ቍጣዬን እፈጽማለሁ፣ በጠላቶቼ ላይ እበቀላለሁ። 25 እጄንም በአንቺ ላይ አመጣለሁ፣ ዝገትሽንም በጣም አነጻለሁ፣ አለመንጻትሽንም ሁሉ አወጣለሁ፤ 26 ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ፣ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያው ጊዜ መልሼ አስነሣለሁ፤ ከዚያም በኋላ የጽድቅ ከተማ፣ የታመነችም ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።" 27 ጽዮን በፍርድ፣ ከእርሷም በንስሃ የሚመለሱ በጽድቅ ይድናሉ። 28 በደለኞችና ኃጢአተኞች ግን በአንድነት ይሰበራሉ፣ እግዚአብሔርንም የሚተዉ ይጠፋሉ። 29 "በተመኛችኋት የተቀደሰች የአድባር ዛፍ ታፍራላችሁና፣ በመረጣችኋትም አትክልት ስፍራ ላይ እፍረት ይይዛችኋልና፤ 30 ቅጠልዋ እንደ ረገፈ ዛፍ፣ ውሃም እንደሌለባት አትክልት ትሆናላችሁና። 31 ኃይለኛውም እንደ ተልባ ጭረት፣ ሥራውም እንደ ጠለሸት ይሆናል፤ አብረውም ይቃጠላሉ፣ እነርሱንም የሚያጠፋ የለም።"