1 የይሁዳ ነገሥታት ዖዝያን፣ ኢዮክታም፣ አካዝና ሕዝቅያስ በነገሡበት ዘመን ስለ ይሁዳ ለአሞጽ ልጅ ለኢሳይያስ ያህዌ የሰጠው ራእይ፡፡ 2 ያህዌ እንዲህ ይላልና ሰማያት ሆይ ስሙ፤ ምድርም አድምጪ፤ ‹‹ልጆች አሳደግሁ፤ እነርሱ ግን ዐመፁብኝ 3 በሬዎች ባለቤታቸውን ያውቃሉ፤ አህዮችም የሚመግባቸውን ያውቃሉ፤ እስራኤል ግን አያውቅም፤ እስራኤልም አያስተውልም፡፡›› 4 በዚህ በኀጢአተኛ ሕዝብ፣ በዚህ የኀጢአት ሸክም በተጫነው የክፉ አድራጊዎች ትውልድ፣ ዐመፀኞች ልጆች ላይ ክፉ ነገር ይመጣል፡፡ የእስራኤልን ቅዱስ ያህዌን ትተዋል፤ ከእርሱም ዘወር ብለዋል፡፡ 5 የያህዌን ቅጣት የሚያመጣባችሁን ነገር የምታደርጉት ለምንድነው? በእርሱ ላይ የምታምፁት ለምንድነው? እናንተ አእምሮና ልቡ እንደ ታመመ ሰው ናችሁ 6 ከእግር ጥፍር ጀምሮ እስከ ራስ ጠጉር ድረስ ጤናማ አካል የላችሁም፡፡ ቁስልና እባጭ፣ መግልም ሞልቶበታል፤ ቁስላችሁ አልታጠበም፤ አልታሰረም፤ በዘይትም አልለዘበም፡፡ 7 ጠላት አገራችሁን አጥፍቷል፤ ከተሞቻችሁን አቃጥሎአል የተረፈም የለም፡፡ ዐይናችሁ እያየ እርሻችሁ ላይ ያለውን እህል ባዕዳን ይዘርፋሉ፤ ዐይናቸው የሚያርፍበትን ነገር ሁሉ ያጠፋሉ፡፡ 8 የኢየሩሳሌም ከተማ እንደ እረኛ ጐጆ አንሳለች፤ የወይን እርሻ ላይ እንዳለ መጠለያ፣ በዱባ ተክል ውስጥ እንዳለ ጐጆና በጠላት እንደ ተከበበች ከተማ ሆናለች፡፡ 9 የሰራዊት ጌታ ያህዌ ከሕዝቡ ጥቂቱን ባያተርፍልን ኖሮ፣ እንደ ሰዶምና ገሞራ ከተሞች ሁላችንም እንጠፋ ነበር፡፡ 10 እናንተ የሰዶም ገዦች ያህዌ የሚነግራችሁን ስሙ! እናንተ የገሞራ ሰዎች የአምላካችንን ሕግ አድምጡ! 11 ‹‹የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይረባኛል?›› ይላል ያህዌ፤ የአውራ በጐች ወይም የሰቡ እንቦሳዎችን የሚቃጠል መሥዋዕት አልፈልግም፡፡ የእንቦሳዎች፣ የበጐች ወይም የፍየሎች ደም ደስ አያሰኘኝም፡፡ 12 እነዚህን ሥርዐቶች ሁሉ እየፈጸማችሁ እኔን ለማምለክ እንድትመጡና የመቅደሴን አደባባይ እንድትረግጡ የነገራችሁ ማን ነው? 13 ለእኔ ምንም ስለማይጠቅመኝ እነዚህን መባዎች አታምጡ! ካህናት የሚያቀርቡትን ዕጣን እጸየፋለሁ! የወር መባቻችሁን፣ ሰንበቶቻችሁንና በዓሎቻችሁን ከዐመፃችሁ የተነሣ እጠላለሁ፡፡ 14 የወር መባቻችሁንና በዓሎቻችሁን ሁሉ ጠልቻለሁ፤ እንደ ከባድ ሸክምም ሆነውብኛል፡፡ 15 ወደ እኔ ለመጸለይ እጆቻችሁን ስታነሡም ወደ እናንተ አልመለከትም፤ ዘወትር ወደ እኔ ብትጸልዩም አልሰማችሁም፤ ምክንያቱም እጆቻችሁ በገደላችኋቸው ሰዎች ደም ተበክለዋል 16 ልባችሁን ታጥባችሁ ንጹሕ ሁኑ፣ ክፉ ሥራችሁን ሁሉ አስወግዱ፡፡ 17 መልካምን ማድረግ ተማሩ፤ ሰዎች እውነትን እንዲያደርጉ አስተምሩ የተበደሉትን ታደጉ፤ ለድኻ አደጐችና ለመበለቶች ተሟገቱ፡፡›› 18 ያህዌ እንዲህ ይላል፤ ‹‹የምታደርጉትን አስቡ፤ ኀጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እነደ ደም ቢቀላም፣ እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል፡፡ 19 ለእኔ ብትታዘዙ፤ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ 20 እምቢ ብትሉኝና ብታምፁ ግን የጠላቶቻችሁ ሰይፍ ይበላችኋል›› ያህዌ ተናግሮአልና ይህ ይሆናል፡፡ 21 እናንተ የኢየሩሳሌም ሰዎች በአንድ ወቅት ያህዌን ብቻ በታማኝነት ታመልኩ ነበር፤ አሁን ግን ለባልዋ ታማኝ እንዳይደለች አመንዝራ ሆናችኋል፡፡ ነዋሪዎቹ ሁልጊዜ እውነትና ጽድቅ ያደርጉ ነበር አሁን ግን ከተማችሁ በነፍሰ ገዳዮች ተሞልታለች፡፡ 22 ብራችሁ ከእንግዲህ ንጹሕ አይደለም፡፡ ወይን ጠጃችሁ ከውሃ ጋር ተደባልቆአል፡፡ 23 መሪዎቻችሁ ዐመፀኞችና የሌቦች ግብረ አበር ሆኑ፡፡ ሁሉም ገንዘብ ማግኘትና አድልዎ ለማድረግ ስጦታ ይፈልጋሉ፡፡ ለድኻ አደጐች አይቆሙም፤ መበለቶችንም መርዳት አይፈልጉም፡፡ 24 ስለዚህ የሰራዊት ጌታ ያህዌ፣ የእስራኤል ኀያል እንዲህ ይላል፤ ‹‹ተቃዋሚዎቼን እበቀላለሁ፤ ጠላቶቼንም እቀጣለሁ፡፡ 25 እጄን በእናንተ ላይ አነሣለሁ በጽኑ ቁጣም እቀጣችኋለሁ፡፡ ዝገታችሁን ለማስወገድ እንደ ብር አነጥራችኋለሁ፡፡ 26 ከዚያ በኋላ እንደ ጥንቱ መልካም ፈራጆችን እሰጣችኋለሁ፤ እንደ ጥንቱ ዘመን መልካም መካሪዎች ይኖሩዋችኋል፡፡ ሰዎች ከተማችሁን የጽድቅ ከተማ፣ የታመነች ከተማ ብለው ይጠሩዋታል፡፡›› 27 የኢየሩሳሌም ሰዎች ቅን የሆነውን በማድረጋቸው ያህዌ ከተማቸውን ይጠግናል፤ ንስሐ የሚገቡትንም በጽድቃቸው ያድናቸዋል፡፡ 28 ዐመፀኞችና ኀጢአተኞችን ግን ያደቅቃል እርሱን የሚተውም ይጠፋሉ፡፡ 29 የተቀደሱ ከምትሏቸው ወርካዎች በታች ጣዖቶችን በማምለካችሁ ታፍራላችሁ ደስ ተበሰኛችሁባቸው አትክልት ቦታዎችም ለጣዖቶች በመስገዳችሁ ትዋረዳላችሁ፡፡ 30 ቅጠሉ እንደ ጠወለገ ታላቅ ወርካ፣ ውሃ ከማጣቱ የተነሣ እንደ ደረቀ አትክልት ቦታ ትሆናላችሁ፡፡ 31 ከእናንተ ብርቱዎች እንደ ደረቅ እንጨት ይሆናሉ ሥራቸውም እንደ ብልጭታ ይሆናል፡፡ እነርሱም ሆነ፣ ክፉ ሥራቸው ይቃጠላሉ እሳቱንም የሚያጠፋው የለም፡፡››