ምዕራፍ 1

1 አስቀድሞ እግዚአብሔር በተለያዩ መንገዶች በነቢያት አንደበትና መጻሕፍት ለአባቶቻችን ተናገረ፡፡ 2 አሁን በመጨረሻው ዘመን መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር በልጁ በኩል ተናገረን፡፡ ሁሉ የእርሱ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር እርሱን መርጦታል፡፡ ዓለማትንም እንደዚሁ በእርሱ ፈጥሯል፡፡ 3 ልጁ የእግዚአብሔር አስደናቂ ኃይል ማሳያ ነጸብራቅ ነው፡፡ እርሱ በትክክል እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል አጥርቶ ያሳያል፡፡ የተፈጠሩት ነገሮች ሁሉ መኖራቸውን እንዲቀጥሉ የሚያደርገው ኃይል ባለው ትእዛዙ ነው፡፡ ኃጢአትን ሁሉ ካነጻ በኋላ ወደ ሰማይ አርጎ እና በክብር ከፍ ብሎ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል፡፡ በዚያም ከአባቱ ጋር ይገዛል፡፡ 4 ስሙና ሥልጣኑ ከእነርሱ እጅግ የላቀ እንደሆነ ሁሉ እግዚአብሔር ልጁን ከመላእክት በእጅጉ ከፍ አድርጎታል፡፡ 5 እግዚአብሔር ለልጁ የተናገረውን ለሌላ ለየትኛውም መላእክ ስለመናገሩ በቅዱስ መጻሕፍት አልተጻፈም፡፡ “አንተ ልጄ ነህ! እኔም ዛሬ ወልጄሀለሁ!” በሌላ መጽሐፍም ይህንን ብሏል፡፡ “እኔ አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል፡፡” 6 የከበረው አንድ ልጁ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ እግዚአብሔር፡- “መላእክት ይስገዱለት” ብሎ አዝዟል፡፡ 7 በቅዱሳት መጻሕፍትም ስለ መላእክቱ ይህ ተጽፏል፡- “እግዚአብሔር መላእክቱን እንደ እሳት ነበልባል በኃይል እርሱን የሚያገለግሉ መናፍስት አድርጓቸዋል፡፡” 8 ስለ እግዚአብሔር ልጅ ግን እንዲህ ተጽፏል፡፡ “አንተ ለዘላለም የምትገዛ አምላክ ነህ፤ በመንግሥትህ ላይ በጽድቅ ትነግሣለህ፡፡ 9 የሰዎችን የጽድቅ ሥራ ወደድህ፣ ኃጢአታዊ ሥራቸውን ጠላህ፡፡ ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር ከሌሎች ይልቅ በደስታ ሞላህ፡፡” 10 በሌሎች መጻሕፍትም ልጁ ከመላእክት ከፍ ስለማለቱ እንደተጻፈ እናውቃለን፡፡ “ጌታ ሆይ፣ በመጀመሪያ ምድርን የፈጠርህ አንተ ነህ፡፡ ከዋክብትንና በሰማይ ያሉትን ጨምሮ የተቀሩትንም ዓለማት ሠራህ፡፡” 11 እነርሱ ያልፋሉ፤ አንተ ግን ለዘላለም ትኖራለህ፡፡ ልብስ እንደሚያረጅ እነርሱ እንደዚያ ያረጃሉ፡፡ 12 እንደ ድሪቶ ልብስ ትጠቀልላቸዋለህ፡፡ ሰው ያረጀውን ልብሱ እንደሚለውጥ ሁሉ አንተም በአዲስ ትተካቸዋለህ፡፡ አንተ ግን አትለወጥም፤ ዘላለማዊ ነህ!” 13 እግዚአብሔር ለልጁ የተናገረውን ለመላእክት አልተናገረም፡፡ “ጠላቶችህን ሁሉ ሳሸንፍልህ አንተ አብረኸኝ ለመግዛት በቀኜ ተቀመጥ!” 14 መላእክት እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ሊያድናቸው ቃል የገባላቸውን አማኞች እንዲያገለግሉ የላካቸው መናፍስት ናቸው፡፡