ምዕራፍ 1

1 በአርጤክስስ ዘመን (እርሱም ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በአንድ መቶ ሃያ ሰባት አገሮች የነገሠው ነው) 2 በእነዚያ ጊዜያት ንጉሡ አርጤክስስ በሱሳ ግንብ ውስጥ ባለው የመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀመጠ። 3 በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለሹማምንቱና ለአገልጋዮቹ በሙሉ ግብዣ አደረገላቸው። የፋርስና የሜዶን የጦር አዛዦች፥ ባላባቶችና የአውራጃ አስተዳዳሪዎችም በፊቱ ነበሩ። 4 የመንግሥቱን ውበት ባለጸግነትና የግርማውን ክብር ታላቅነት ለብዙ ቀናት ማለትም ለ180 ቀናት አስጎበኛቸው። 5 እነዚህ ቀናት ካበቁ በኋላ ንጉሡ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ግብዣ አዘጋጀ። ግብዣው የተዘጋጀው ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በሱሳ ቤተመንግሥት ውስጥ ለነበሩት ሰዎች ሁሉ ነበር። ይህም የተደረገው በንጉሡ ቤተመንግሥት መናፈሻ በሚገኘው አደባባይ ውስጥ ነበር። 6 ከጥጥ የተሠሩ ነጭና ሰማያዊ መጋረጃዎች ነጭና ሐምራዊ ገመድ በብር ቀለበቶቹ ውስጥ አልፈው በእምነበረዱ ቋሚዎች ላይ በመሰቀላቸው የመናፈሻው አደባባይ ተውቦ ነበር። በቀይ ዓለት፥ በእምነበረድ፥ በእንቁ እናትና የተለያየ ቀለም ባላቸው የንጣፍ ድንጋዮች ባሉት ሥዕላዊ ወለል ላይ የወርቅና የብር ድንክ አልጋዎች ነበሩ። 7 መጠጡ በወርቃማ መጠጫዎች ይቀርብ ነበር። እያንዳንዱ መጠጫ የተለያየ ነበር፥ ከንጉሡ ለጋስነት የተነሣም የቤተመንግሥቱ ወይን የተትረፈረፈ ነበር። 8 መጠጡ ይቀርብ የነበረውም፥ "ግዴታ መኖር የለበትም" የሚለውን መመሪያ በመከተል ነበር። እንግዶቹ እያንዳንዳቸው በሚፈልጉት መጠን እንዲቀርብላቸው ንጉሡ የቤተመንግሥቱን ሠራተኞች አዝዞ ነበር። 9 ንግሥት አስጢን በበኩሏ በንጉሡ አርጤክስስ ንጉሣዊ ቤተመንግሥት ለሴቶች ግብዣ አደረገች። 10 በሰባተኛው ቀን ንጉሡ ከወይን ጠጅ የተነሣ ልቡን ደስታ በተሰማው ጊዜ ምሁማንን፥ ባዛንን፥ ሐርቦናን፥ ገበታን፥ ዘቶልታን፥ ዜታርንና ከርከስን (በፊቱ የሚያገለግሉትን ሰባቱን ሹማምንት) ንግሥት አስጢን ዘውዷን ደፍታ በፊቱ እንድትቀርብ አዘዛቸው። 11 ተክለ ሰውነቷ ያማረ ነበርና ውበቷን ለሕዝቡና ለሹማምንቱ ለማሳየት ፈለገ። 12 ንግሥት አስጢን ግን ንጉሡ በሹማምንቱ በላከባት ቃል መሠረት ለመምጣት እምቢ አለች። ከዚያም ንጉሡ በጣም ተቆጣ፥ ቁጣውም በውስጡ ነደደ። 13 ስለዚህ ንጉሡ ዘመኑን ከሚመረምሩ ጥበበኞች ሰዎች ጋር ተመካከረ (ሕግንና ዳኝነትን ስለሚያውቁት ሰዎች ሁሉ የንጉሡ ልምድ እንዲህ ነበርና)። 14 የቅርቦቹ የነበሩትም ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መሳፍንት የሆኑት አርቄስዮስ፥ ሼታር፥ አድማታ፥ ተርሺሽ፥ ሜሬስ፥ ማሌሴዓርና ምሙካን ነበሩ። እነዚህ ለንጉሡ የሚቀርቡና በመንግሥቱ ውስጥ ከፍተኛውን ሥልጣን የያዙ ናቸው። 15 "በሹማምንቱ የተላከባትን የንጉሡን የአርጤክስስን ትዕዛዝ አልታዘዘችምና በሕጉ መሠረት በንግሥት አስጢን ላይ መደረግ ያለበት ምንድነው?" 16 ምሙካንም በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት እንዲህ አለ፥ "ንግሥቲቱ አስጢን የበደለችው መኳንንቱን ሁሉና በንጉሡ በአርጤክስስ ግዛቶች ሁሉ የሚገኘውን ሕዝብ በሙሉ ደግሞ እንጂ ንጉሡን ብቻ አይደለም። 17 የንግሥቲቱ ጉዳይ በሁሉም ሴቶች የሚታወቅ ይሆናል። ይህም ባሎቻቸውን እንዲንቁ ያደርጋል። እነርሱም፥ 'ንግሥት አስጢንን በፊቱ እንዲያቀርቧት ንጉሡ አርጤክስስ አዘዘ፥ እርስዋ ግን እምቢ አለች' ይላሉና። 18 የንግሥቲቱን ጉዳይ የሰሙ የመኳንንቱ ሚስቶችም ይህ ቀን ከማለፉ በፊት ለንጉሡ መካንንቶች በሙሉ ተመሳሳዩን ቃል ይናገራሉ። ብዙ ንቀትና ቁጣም ይሆናል። 19 ንጉሡን ደስ የሚለው ከሆነ፥ አስጢን ዳግመኛ በፊቱ እንዳትቀርብ ንጉሣዊ ትዕዛዝ ያውጣ፥ ሊለወጥ የማይቻል ሆኖም በፋርስና በሜዶን ሕግ ውስጥ ይጻፍ። የንግሥትነቷን ክብርም ንጉሡ ክእርስዋ ለምትሻል ለሌላይቱ ይስጥ። 20 የንጉሡ ትዕዛዝ በሰፊው መንግሥቱ ሁሉ በሚታወጅበት ጊዜ፥ ከታላቁ እስከ ታናሹ ድረስ ሚስቶች ሁሉ ባሎቻቸውን ያከብራሉ።" 21 ንጉሡና መካንንቶቹ በዚህ ምክር ተደሰቱ፥ ንጉሡም የምሙካንን ምክር ተግባራዊ አደረገው። 22 እርሱም ደብዳቤዎችን ለእያንዳንዱ አውራጃ በየራሱ ጽሕፈትና ለእያንዳንዱ ሕዝብ በየራሱ ቋንቋ አድርጎ ወደ መንግሥቱ አውራጃዎች በሙሉ ላከው። እርሱም እያንዳንዱ በቤተሰቡ ላይ ገዥ እንዲሆን አዘዘ። ይህም ትዕዛዝ በመንግሥቱ ውስጥ ላለ ለእያንዳንዱ ሕዝብ በየቋንቋው ተሰጠው።