ምዕራፍ 1

1 ንጉሥ ኢዮአቄም በይሁዳ ላይ ሦስት ዓመት ያህል እንደ ገና፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከተማይቱን ከመውጋቱ በፊት እንድትዳከም ያደረጋት ዘንድ ከሠራዊቱ ጋር መጥቶ ኢየሩሳሌምን ከበባት። 2 ከሁለት ዓመት በኋላ እግዚአብሔር ለናቡከደነፆር ወታደሮች በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአቄም ላይ ድልን ሰጣቸው። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበሩትን እንዳንድ ንዋያተ ቅድሳትንም በሰናዖር ምድር ወዳለችው ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ በዚያም ናቡከደነፆር በጣዖቱ ግምጃ ቤት አኖራቸው። 3 ከዚያ በኋላ ወታደሮቹ ወደ ባቢሎን ካመጧቸው እስራኤላውያን ወንዶች አንዳንዶቹን ወደ እርሱ እንዲያመጧቸው ናቡከደነፆር በቤተ መንግሥቱ የሹማምንት አለቃ የሆነውን አስፋኔዝን አዘዘው፤ እነዚህ ወንዶች የይሁዳ ንጉሣዊ ቤተ ሰብን ጨምሮ የአንዳንድ ታዋቂ ቤተ ሰቦች ወገን ነበሩ። 4 ናቡከደነፆር የፈለገው በጣም ጤናማዎች፣ መልከ መልካሞች፣ ጠቢባን፣ በሚገባ የተማሩ፣ በቤተ መንግሥት ለማገልገልም ችሎታ የነበራቸውን ወንዶች ብቻ ነበር፤ የባቢሎናውያንን ሥነ ጽሑፍ መረዳት እንዲችሉ የባቢሎንን ቋንቋ እንዲያስተምራቸው ፈለገ። 5 ንጉሡ አገልጋዮቹን፣ “ለእኔ የሚቀርበውን ምርጥና ከፍተኛ ጥራት ያለው ምግብና ወይን ጠጅ ሰጧቸው፤ ለሦስት ዓመት ካሠለጠናችኋቸው በኋላ አገልጋዮቼ ይሆናሉ” ብሎ አዘዛቸው። 6 ከተመረጡት እስራኤላውያን ወጣት ወንዶች መካከል ሁላቸውም ከይሁዳ ወገን የነበሩት ዳንኤል፣ ሐናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ። 7 አስፋኔዝም ዳንኤልን ብልጣሶር፣ ሐናንያን ሲድራቅ፣ ሚሳኤልን ሚሳቅ፣ አዛርያንም አብደናጎ ብሎ በመሰየም ባቢሎናዊ ስም አወጣላቸው። 8 ዳንኤል ግን በመንጻት ሕግ ሥርዓት የሚያረክሰው በመሆኑ፣ ንጉሡ የሚበላውን ምግብ ላለመብላት፣ ንጉሡ የሚጠጣውንም ወይን ጠጅ ላለመጠጣት ወሰነ፤ ስለዚህ ራሱን እንዳያረክስ ሌላ ዐይነት ምግብ እንዲበላና ሌላ ዐይነት መጠጥ እንዲጠጣ ይፈቅድለት ዘንድ የንጉሡን ሹማምንት አለቃ እስፋኔዝን ጠየቀ። 9 ከአስፋኔዝ ጋር በነ በረውም ግንኙነት እግዚአብሔር ለዳንኤል ደግነትና ርኅራኄ እንዲኖረው አደረገ፤ የሹማምንቱ አለቃም ለዳንኤል ትልቅ አክብሮት ነበረው። 10 ዳንኤልንም እንዲህ አለው፦ “የምትበሉትና የምትጠጡት ምን መሆን እንደሚገባው ጌታዬ ንጉሡ መርጦላችኋል፤ ሌላ ምግብ በልታችሁ እኩዮቻችሁ ከሆኑት ከሌሎቹ ወጣቶች ይልቅ ብትከሱና ብትገረጡ፤ መመሪያውን ስላልተከተላችሁ፣ ወታደሮቹን ያዝና ራሴን ያስቀላኛል።” 11 የመኳንንቱ አለቃ ለዳንኤል፣ ለሐናንያ፣ ለሚሳኤልና ለአዛርያ ምግባቸውንና መጠጣቸውን እንዲሰጣቸው አንድ አገልጋይ መደበ። ዳንኤልም አገልጋዮን አነጋገረው፤ 12 እንዲህም አለው፦ “ለዐሥር ቀናት የምንበላውን አትክልትና የምንጠጣውን ውሃ ብቻ በመስጠት እኛን አገልጋዮችን ፈትነን! 13 ከዐሥር ቀናት በኋላ ጤናማዎች መሆን አለመሆናችንን፣ እንደዚሁም የንጉሡን ምግብ የሚበሉትም ምን እንደሚመስሉ ተመልከት። ከዚያም መልካም የመሰለህን አድርግብን።” 14 አገልጋዩ በዚህ ፈተና ተስማምቶ ለዐሥር ቀናት ዳንኤል የጠየቀውን ምግብ ሰጣቸው። 15 ከዐሥር ቀን በኋላ ንጉሡ የመረጠላቸውን ምግብ ሲመገቡ ከነበሩት ወጣቶች ሁሉ እነርሱ ይበልጥ ጤናሞችና ያማረባቸው ሆነው ተመለክታቸው። 16 ከዚያ በኋላ የንጉሡን ልዩ ምግብና ወይን ጠጅ አስቀርቶ፣ የሚመገቡትን አትክልት ብቻ ሰጣቸው። 17 እግዚአብሔርም ለእነዚህ አራት ወጣቶች ባቢሎናውያን የጻፏቸውንና ያጠኗቸውን ብዙ ነገሮች እንዲያጠኑ ጥበብና ማስተዋል ሰጣቸው። ለዳንኤል ደግሞ ራእይንና ሕልምን የመተርጎም ችሎታ ሰጠው። 18 ከሦስት ዓመታት በኋላ ንጉሡ በሥልጠና ላይ የነበሩት በፊቱ የሚቀርቡትን ቀን ወሰነ። የንጉሡ ሹማምንት አለቃ የነበረው አስፋኔዝ ሁሉንም ወስዶ በናቡከደነፆር ፊት አቀረባቸው። 19 ንጉሡ አነጋገራቸውና ከሌሎቹ መካከል እንደ ዳንኤል፣ ሐናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ችሎታ ያለው አንድም ወጣት እንዳልነበረ ዐወቀ። 20 ጥበብንና ማስተዋልን በሚጠይቁ ጕዳዮች ሁሉ ከአስማተኞቹና ሙታን ሳቢዎች ነን ከሚሉት ይልቅ እርሱን በማማከር በኩል እነዚህ ዐሥር ጊዜ ብልጫ ያለው ውጤታማ ምክር የሚሰጡ ሆነው አገኛቸው፤ በመንግሥቱ ሁሉ ከእነዚህ ከአራቱ የተሻለ ማንም አልነበረም። 21 ቂሮስ እስከ ነገሠበት እስከ መጀመሪያው ዓመት ድረስ ከስድሳ ዓመት በላይ ዳንኤል ንጉሡን እያገለገለ ቆየ።