ምዕራፍ 1

1 አንተ እኔን ሽማግሌውን ዮሐንስን ታውቀኛለህ፡፡ ወዳጄ ጋይዩስ ሆይ፣ ይህን ደብዳቤ በዕውነት ለምወድህ ለአንተ እጽፍልሃለሁ፡፡ 2 ወዳጄ ሆይ፣ በሁሉም መንገድ ነገሮች መልካም እንዲሆንልህ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፣ እናም ከእግዚአብሔር ጋር ያለህ ነገር ጤናማ እንደሆነ ጤናህም የተጠበቀ እንዲሆን እጸልያለሁ፡፡ 3 አንዳንድ አማኞች ወደዚህ መጥተው በክርስቶስ እውነተኛ መልዕክት እንደምትኖር ስለነገሩኝ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ከእግዚአብሔር እውነት ጋር የሚስማማ ህይወት እየኖርክ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ 4 በክርስቶስ እንዲያምኑ የረዳኋቸው ሰዎች ከእግዚአብሔር እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ እየኖሩ እንደሆነ ስሰማ በጣም ደስ ይለኛል! 5 ወዳጆች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ስራ ለመስራት የሚደክሙትን አማኞች፣ ሌላው ቀርቶ የማታውቋቸውን እንግዶች እንኳን ለመርዳት ነገሮችን ስታደርጉ ኢየሱስን በታማኝነት ማገልገላችሁ ነው፡፡ 6 አንዳንዶቹ እዚህ ባለው ጉባኤ ፊት እንዴት እንደምትወዳቸው ተናግረዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ስራቸውን እግዚአብሔርን በሚያከብር መንገድ እንዲሰሩ መርዳትህን መቀጠል አለብህ፡፡ 7 እነዚያ አማኞች ለሰዎች ስለ ኢየሱስ ለመናገር ሲሄዱ፣ በክርስቶስ ከማያምኑ ሰዎች ምንም ገንዘብ አይቀበሉም፡፡ 8 ስለዚህ እኛ በክርስቶስ የምናምን የእግዚአብሔር መልዕክት ከሚሰብኩ ጋር አብሮ ለመስራት እንደዚህ ላሉ ሰዎች ምግብና ገንዘብ ልንሰጣቸው ይገባል፡፡ 9 እነዚያን አማኝ ወገኖች እንዲረዱ ለእናንተ ማህበረ ምዕመናን ደብዳቤ ጽፌ ነበር፡፡ ሆኖም፣ ዲዮጥራጢስ ደብዳቤዬን አልተቀበለም፣ ምክንያቱም እርሱ በእናንተ ላይ የበላይ መሆን ይፈልጋል፡፡ 10 ስለዚህ እዚያ ስመጣ ለሁሉም እርሱ ያደረገውን ክፉ ስራ እናገራለሁ፡ በንግግሩ እኛን ለመጉዳት የማይረቡ ክፉ ነገሮችን ለሰዎች ያወራሉ፡፡ ይህንን በማድረግ ብቻ አያበቃም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ስራ ለመስራት የሚደክሙትን ይቃወማል፡፡ ደግሞም እነርሱን ሊቀበሏቸው የሚወዱትን ከጉባኤ ለቀው እንዲወጡ በማድረግ እንዳይሰሩ ይከለክላቸዋል፡፡ 11 ወዳጆቼ ሆይ፣ እንደዚህ ያለውን መጥፎ ምሳሌነት አትምሰሉ፡፡ ይልቁንም፣ ጥሩ ምሳሌነቶችን ተከተሉ፡፡ መልካም የሚያደርጉ ከእግዚአብሔር እንደሆኑ አስታውሱ፡፡ ደግሞም መጥፎ የሆነውን በማድረግ የሚጸና እግዚአብሔርን አያውቅም፡፡ 12 ድሜጥሮስን የሚያውቁ አማኞች ሁሉ እርሱ መልካም ሰው መሆኑን ይመሰክሩለታል፡፡ እውነት ራሷ ሰው ብትሆን፣ተመሳሳይ ነገር ትናገርለታለች! እኛም ደግሞ ድሜጥሮስ መልካም ሰው መሆኑን እንመሰክራለን፣እናንተም እኛ ስለ እርሱ የምንናገረው እውነት እንደሆነ ታውቃላችሁ፡፡ 13 ይህን ደብዳቤ መጻፍ ስጀምር፣ ልነግራችሁ ያሰብኩት ብዙ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን በደብዳቤ ልገልጸው አልፈልግም፡፡ 14 ይልቁንም፣ በቅርቡ መጥቼ ላያችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ፊትለፊት ተገናኝተን እንነጋገራለን፡፡ 15 እግዚአብሔር ሰላሙን እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፡፡ በዚህ የሚገኙ ወዳጆቻችን ሰላምታ ያቀርቡችኋል፡፡