1 እኔ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፍኩት መልእክት፡፡ ክርስቶስ ከእርሱ ጋር አንድ ለሚሆኑ ሁሉ እግዚአብሔር አሁንና ለዘለዓለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው ቃል ስለመግባቱ ለሰው ሁሉ እንድመሰክር ሐዋርያ አድርጎ ላከኝ፡፡ 2 ጢሞቴዎስ፡- እንደራሴ ልጅ አድርጌ እወድሃለሁ፡፡ አባታችን እግዚአብሔር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቸርነቱን፣ ሰላሙንና ምህረቱን ያብዛልህ፡፡ 3 አባቶቼ ያደርጉ እንደነበረው እግዚአብሔርን የእርሱን ፈቃድ በእውነት በመፈለግ አገለግለዋለሁ፣ አመሰግነዋለሁም፡፡ ጢሞቴዎስ ሆይ፣ ሁልጊዜ ቀንና ሌሊት ስለ አንተ እጸልያለሁ፡፡. 4 እንባህን እያሰብሁኝ ደግሜ ላይህ እናፍቃለሁ፡፡ ደግሜ ባይህ ደስታዬ እጅግ የላቀ ይሆናል፡፡. 5 በአንተ ያለውን በኢየሱስ ላይ ያለህን እውነተኛ እምነት አስታውሳለሁ፡፡ በመጀመርያ አያትህ ሎይድና እናትህም ኤውንቄ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰጡ፣ በእነርሱ እንደነበረው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እውነተኛ እምነት በአንተም ውስጥ መኖሩን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ 6 እምነትህ በኢየሱስ ላይ ስለሆነም እጄን ጭኜ በጸለይሁልህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰጠህን ስጦታ እንድትጠቀምበት አሳስብሃለሁ፡፡ 7 እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠው መንፈስ ፍርሃት እንዲሰማን የሚያደርግ ሳይሆን ይልቁንም እግዚአብሔርን ለመታዘዝ፣ እርሱንና ባልንጀራዎቻችንን እንድንወድ ራሳችንንም እንድንገዛ የሚያደርግ መንፈስ ነው፡፡ 8 ስለዚህም ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሌሎች ለመመስከር አትፈር፡፡ የእኔ ወዳጅም በመሆንህ አትፈር፣ ወህኒ ቤት ያለሁት በኢየሱስ በማመኔ ነውና፡፡ ይልቅም ለሌሎች ወንጌልን በመናገር ሊመጣብህ ያለውን መከራ መቀበል ትችል ዘንድ ፈቃደኛ ሁን፡፡ እግዚአብሔርም ስለ እርሱ የምትቀበለውን መከራ ሁሉ እንድትሸከም ያስችልሃል፡፡ 9 እንዲህ የሚያደርገውም እርሱ ስላዳነንና የእርሱ እንድንሆን ስለጠራን ነው፡፡ እግዚአብሔር ያዳነን መልካምን ነገር አድርገን ሳይሆን ድነትን ለእኛ ስጦታ አድርጎ ስለሰጠን ነው! ዓለም ሳይፈጠን በመሲሁ በኢየሱስ በኩል ይህን ስጦታ ለእኛ ሰጠን፡፡ 10 አሁን ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር እነርሱን ማዳን እንደሚችል ማየት ችለዋል ምክንያቱም አዳኛችን መሲሁ ኢየሱስ ወደ ምድር መጥቶ ሞትን በማሸነፍ ሰዎች ለዘላለም ሕይወት እንዲኖራቸው የሚያደርገውን እውነት ይኸውም ወንጌልን ገልጧል፡፡ 11 እግዚአብሔር ሐዋርያ፣ ሰባኪና አስተማሪ እንድሆን የላከኝ በዚህ ምክንያት ነው ፡፡ 12 በአገልግሎቴ ምክንያት መከራን ተቀብያለሁ ነገር ግን አላፍርም ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስን ታምኘዋለሁ፣ በእርሱ ያለኝን እምነት እስከ ሕይወቴ መጨረሻ ድረስ እንደሚጠብቅልኝ አምናለሁ፡፡ 13 በኢየሱስ ክርስቶስ ባለህ እምነትና ፍቅር ከእኔ የሰማኸውን እውነተኛ ትምህርት ተከተል፡፡ 14 እግዚአብሔር ለአንተ የሰጠውን መልካም ዜና ለሰዎች እንትሰብክ አደራ ሰጥቶሃል፡፡ የተሰጠህን መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ላይ በመደገፍ ጠብቀው፡፡ 15 በእስያ ያሉት አማኞች በሙሉ ፊሎጎስና ሄርዋጌኔስም ጭምር እንደተዉኝ ታውቃለህ፡፡ 16 እኔ ግን ጌታ ለሄኔሲፎሩ ቤተሰቦች ምህረትን እንዲያደርግ እጸልያለሁ፡፡ በተደጋጋሚ አግዞኛል፣ እስረኛ በመሆኔም አላፈረብኝም፡፡ 17 ወደ ሮም በመጣ ጊዜ እኔን ለማግኘት ብዙ ደክሞ ፈልጎ አግኝቶኛል፡፡ 18 ጌታ በቀናት መጨረሻ ለሄኔሲፎሩ ምህረትን ያብዛ፡፡ በኤፌሶን እንዴት ያግዘኝ እንደነበር አንተም በሚገባ ታውቃለህ፡፡