ምዕራፍ 1

1 ሳኦል ከሞተ በኋላ፣ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች የአማሌቅን ዝርያዎች ድል አድርገው ወደ ጺቅላግ መንደር ተመለሱ፡፡ በጺቅላግም ሁለት ቀናትን ቆዩ፡፡ 2 በሦስተኛውም ቀን፣ ድንገት በሳኦል ሠራዊት ውስጥ የነበረ አንድ ሰው እዚያ ደረሰ፡፡ ኀዘንተኛ እንደሆነም ለማመልከት ልብሱን ቀድዶ በጭንቅላቱም ላይ አመድ ነስንሶ ነበር፡፡ ወደ ዳዊት መጥቶም አክብሮቱን ለማሳየት በዳዊት ፊት ለፊት ራሱን ከምድር ላይ ጥሎ ሰገደ፡፡ 3 ዳዊትም፡- “ከወዴት መጣህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ሰውየውም ሲመልስ፡- “ከእስራኤላውያን ሠራዊት” አለው፡፡ 4 ዳዊትም፡- “ምን ተፈጥሮ ኖሯል? እባክህ ስለ ጦርነቱ ሁኔታ ንገረኝ” ብሎ ጠየቀው፡፡ ሰውዮውም፡- “የእኛ ሠራዊት ሸሽተው ተበታተኑ፡፡ ከእነርሱም ብዙዎቹ ተገደሉ፡፡ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ሞቱ” ሲል መለሰለት፡፡ 5 ዳዊትም ወጣቱን ሰው፡-“ ሳኦልና ዮናታን አንደ ሞቱ እንዴት ልታውቅ ቻልህ?” አለው፡፡ 6 ወጣቱም ሰው፡- “እኔ ጦርነቱ ይካሄድ በነበረበት በጊልቦዓ ተራራ ነበርሁ፡፡ ሳኦልንም ጦሩን ተመርኩዞ አየሁት፡፡ የጠላት ሠረገላዎችና እነርሱንም የሚያሽከረክሩ ሰዎች በጣም ቀርበውት ነበር፡፡ 7 ሳኦልም ዞር ዞር ብሎ ሲቃኝ እኔን አይቶ ወደ እኔ ተጣራ፡፡ እኔም፡- ‘ምን አደርግ ዘንድ ትሻለህ?’ ብዬ መልስ ሰጠሁት፡፡ 8 እርሱም፡- ‘አንተ ማነህ?’ አለኝ፡፡ እኔም፡- ‘እኔ የአማሌቅ ዝርያ ነኝ’ አልሁት፡፡ 9 ከዚያም እርሱ፡- ‘ወደዚህ መጥተህ ግደለኝ፡፡ እኔ እጅግ ጥልቅ ኅመም ውስጥ ነኝ’ አለኝ፡፡ 10 ስለዚህ ወደ እርሱ ሀጄ ገደልኩት፣ ምክንያቱም በአስከፊ ሁኔታ ቆስሎ ከዚህ በኋላ በሕይወት ሊቆይ እንደማይችል ስለ ተመለከትሁ ነው፡፡ ጌታዬ፣ወደ አንተ ያመጣሁትን ዘውዱንም ከአናቱ ላይ አነሳሁ፣ የክንዱንም አምባር ወሰድሁ፡፡” 11 11 ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች በሙሉ በጣም ማዘናቸውን ለማሳየት ልብሶቻቸውን ቀደዱ፡፡ 12 12 ለሳኦልና ለልጁ ዮናታንም አዘኑ፣ እነርሱም አለቀሱ፣ ፆሙም፣ እስከ አመሻሽ ድረስም እንዲሁ አደረጉ፡፡ 13 13 ነገር ግን ዳዊት ስለ ጦርነቱ ነግሮት የነበረውን ወጣት፡- “አንተ ከወዴት ነህ?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፣ “አባቴ የአማሌቅ ተወላጅ ሲሆን፣ የምንኖረው ግን እስራኤል ውስጥ ነው” ብሎ መለሰለት። 14 ዳዊትም እንዲህ ሲል ጠየቀው፡- “እግዚአብሔር ንጉሥ ያደረገውን ሰው ሳኦልን ስትገድል፣ ቅጣት ያገኘኛል ብለህ ለምን አልፈራህም? 15 - 16 አንተው ራስህ፡- ‘ጌታ እግዚአብሔር ንጉሥ እንዲሆን የሾመውን ሰው ገድያለሁ ብለሃል፡፡’ ስለዚህ ጥፋተኛ መሆንህን በራስ ላይ መስክረሃል፣ ሞትም ይገባሃል!” አለው፡፡ ከዚያም ዳዊት ከወታደሮቹ አንዱን ወደ እርሱ ጠርቶ፡- “እርሱን ግደለው!” አለው፡፡ ስለዚህ ወታደሩም ገደለው፡፡ 17 ዳዊትም ስለ ሳኦልና ዮናታን ይህንን የሐዘን መዝሙር አቀነባበሮ፣ 18 ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ለይሁዳ ሕዝብ እንዲያስተምሩት አዘዘ፡፡ መዝሙሩም “ቀስቱ” የሚል ስያሜ ተሰጠው፣ ያሻር በሚባለው መጽሐፍ ውስጥም ተጽፎ ተቀመጠ፡፡ መዝሙሩም፡- 19 እናንተ እስራኤላውያን ሰዎች፣ ዝነኛ መሪዎቻችሁ በተራሮች ላይ ተገደሉ! እነዚህ ኃያላን ሰዎች መሞታቸው በጣም ያሳዝናል! 20 ወሬውን በፍልስጥኤም አውራጃዎች ለሚገኙ ጠላቶቻችን አትንገሩ፡፡ በጌታ ከተማም ለሚኖሩ ሕዝብ አትንገሩ፡፡ ሴቶቻቸው ድላቸውን እንዳያከብሩ፣ በአስቀሎና ከተማ ጎዳናዎች ላይም አታውጁ፡፡ እነዚያ አረማዊ ሴቶች ደስ እንዲሰኙ አትፍቀዱላቸው፡፡ 21 ወደፊት በጊልቦዓ ተራሮች ላይ ዝናብም ሆነ ጤዛ ደግሞ እንዳይታይ ምኞቴ ነው እህልም በእነዚያ መስኮች አይብቀል፣ ምክንያቱም የኃያሉ ንጉሥ፣የሳኦል ጋሻ፣በምድር ላይ የወደቀው እዚያ ነው፡፡ አሁንም የሳኦልን ጋሻ በወይራ ዘይት የሚቀባ ማንም የለም፡፡ 22 የዮናታን ቀስቶች ዘወትር ጠላቶቹን ጠልቀው የሚወጉና ደማቸውም እንዲፈስስ የሚያደርጉ አገልጋዮቹ ነበሩ፡፡ የሳኦልም ሠይፍ ዘወትር ጠላቶቹን የሚመታ አገልጋዩ ነበር፡፡ 23 ሳኦልና ዮናታን የተወደዱ ነበሩ፤ ብዙ ሰዎችንም ደስ አሰኝተዋል፡፡ በሕይወት ሲኖሩም ይሁን ሲሞቱ አንድ ላይ ነበሩ፡፡ በጦርነት ውስጥ ከንሥሮች የፈጠኑና ከአንበሶች የበረቱ ነበሩ፡፡ 24 እናንተ በእስራኤል ያላችሁ ሴቶች፣ ስለ ሳኦል አልቅሱ፡፡ እርሱ ውብ የሆኑ ደማቅ ቀይ ልብሶችን የሰጣችሁ ታጌጡባቸው ዘንድ የወርቅ ጌጣጌጦችን የሰጣችሁ ነው፡፡ 25 ወንድሜ ዮናታን መሞቱ በጣም አሳዛኝ ነው እርሱ ኃያል ወታደር ቢሆንም ጠላቶቹ በተራራው ላይ ገደሉት፡፡ 26 ውድ ወዳጄ ዮናታን ስለ አንተ ኀዘንተኛ ነኝ፡፡ አንተ ለእኔ በጣም ውድ ነበርህ፡፡ አንተ አስገራሚ በሆነ ሁኔታ ወደድኸኝ፡፡ እርሱም አንዲት ሴት ባሏን እንዲሁም ልጆቿን ትወድድበት ከነበረው መንገድ እንኳ የላቀ ነበር፡፡ 27 እነዚህ ኃያላን ሰዎች መሞታቸው በጣም አሳዛኝ ነው፣ የእነርሱ ጦር መሣሪያዎችም ከእንግዲህ አይኖሩም!