1 ኢየሱስ ክርስቶስን የማገልገልና እርሱ ሐዋርያ አድርጎ የሾመኝ እኔ ስምዖን ጴጥሮስ ይህን መልእክት ጻፍሁላችሁ፡፡ ይህንን መልእክት የላክሁላችሁም እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ፍጹም ጻድቅ በሆነ በአምላካችንና በአዳኛችን በክርስቶስ እንድናምን እንዳደረገን እናንተም በክርስቶስ እንድታምኑ ነው፡፡ እናንተና እኛ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ተመሳሳይ ክብር ያለን ነን፡፡ እርሱ አምላክ ነው፤ እርሱ ፍጹም ጻድቅ ነው፤ እርሱ እኛ የምናመልከውና አዳኛችንም ነው፡፡ 2 እግዚአብሔርንና ጌታችንን ኢየሱስን በደንብ ስለምታውቁ እግዚአብሔር ምሕረቱን እንዲያበዛላችሁና ጥልቅ የሆነ ሰላሙን እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፡፡ 3 እግዚአብሔር ለዘላለም ለመኖርና እርሱን ለማክበር የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ሰጥቶናል፡፡ ይህንንም ያደረገው በመለኮታዊ ኃይሉ ነው፤ እንዲሁም ይህን ያደረገው እኛ እርሱን ስለምናውቀው ነው፡፡ ደግሞም እርሱ ለእኛ ይህን የሰጠን እርሱን የማወቃችን ውጤት አድርጎ ነው፡፡ ኃያልና መልካም በመሆኑ ምክንያት ሕዝቦቹ እንድንሆን የመረጠን እርሱ ነው፡፡ 4 የማያምኑ ሰዎች እንደሚያደርጉት እንደዚያ ክፉ ነገር በማድረግ እንዳትጠፉ እግዚአብሔር በትክክለኛው መንገድ እንደሚሠራ እናንተም እንደዚያው ትክክል የሆነው ነገር ብቻ ማድረግ መቻል አለባችሁ፡፡ እርሱ እጅግ ታላቅና በዋጋ የማይተመንን ነገር እንደሚያደርግልን በገባልን ቃል መሠረት ያደርገዋል፡፡ 5 እግዚአብሔር ይህንን ሁሉ ስላደረገልን በክርስቶስ ለማመን ብቻ ሳይሆን መልካም ምስክርነት ያለው ኑሮ ለመኖር የቻላችሁትን ያህል ጥረት አድርጉ፡፡ ደግሞም መልካም ኑሮ ለመኖር ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን የበለጠ ለማወቅ ጣሩ፡፡ 6 ከዚህ በተጨማሪ እግዚአብሔርን ለማወቅ ጥረት ማድረግ ብቻ ሳይሆን በምታደርጉትና በምትናገሩት ነገምር ራሳችሁን ተቆጣጠሩት፤ በምታደርጉትና በምትናገሩት ራሳችሁን መቆጣጠር ብቻም ሳይሆን ነገር ግን ለእርሱ ታማኞች ሁኑ፤ ለእርሱ መታመን ብቻ ሳይሆን ደግሞም አክብሩት፡፡ 7 እርሱን ማክበር ብቻ ሳይሆን አማኝ ለሆኑ ለሌሎች ወገኖቻችሁ እንደምታስቡላቸው እርግጠኛ ሁኑ፡፡ ለወንድሞችና እኅቶች ማሰብ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ውደዱ፡፡ 8 እነዚህን ብታደርጉና ደግማችሁ ደጋግማችሁ ብታደርጓቸው ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቃችሁ በሕይወታችሁ እጅግ ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ 9 ነገር ግን እነዚህ ነገሮች የሌሏቸው ሰዎች ልክ በዙሪያው ምን እንዳለ ማየት እንደማይችል ዓይነስውር ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ እንኳ አይገነዘቡም፡፡ ዓይኑ በቅርበት ያለውን ብቻ እንደሚያይ ሰው የቅርቡን ምድራዊ ነገር ብቻ ነው የሚያስቡት፡፡ እግዚአብሔር የበፊት ኃጢአታቸውን ይቅር እንዳላቸው ረስተዋል፡፡ 10 እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ከመሆን ይልቅ ሁሉም ሰው እግዚአብሔር የእርሱ ሕዝብ እንድትሆኑ እንደመረጣችሁ የሚያሳዩ ባሕርያት ይኑራችሁ፤ ይህንን ካደረጋችሁ ፈጽሞ በምንም ሁኔታ ከእግዚአብሔር የሚለያችሁ ነገር አይኖርም፤ 11 እናም እግዚአብሔር እናንተን ጌታችንና አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝቡን ለዘላላም ወደሚመራበት መንግሥት በሙሉ ልብ ይቀበላችኋል፡፡ 12 ምንም እንኳን እነዚህ ነገሮች እውነት እንደሆኑ ብታውቁምና አጥብቃችሁ ብታምኑባቸውም ደግሜ ደጋግሜ ላሳስባችሁ ፈልጌያለሁ፡፡ 13 በዚህ ሕይወት እስካለሁ ድረስ ስለ እነዚህ ነገሮች ደጋግማችሁ እንድታስቡ እናንተን መርዳቴ ትክክል ሆኖ ታይቶኛል፡፡ 14 ምክንያቱም ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገለጠልኝ በቅርቡ እንደምሞት አውቄያለሁና፡፡ 15 ከዚህ በተጨማሪም እኔ ከሞትሁ በኋላም ሁልጊዜ እነዚህን ነገሮች ማስታወስ እንድትችሉ እነዚህን ነገሮች ለመጻፍ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ 16 እኛ ሐዋርያቱ የነገርናችሁ እኮ የኢየሱስ ክርስቶስን ኃያልነትና ደግሞ አንድ ቀን ተመልሶ እንደሚመጣ ነው፡፡ ይህንንም ስንነግራችሁ እኛ ራሳችን በገዛ ዓይኖቻችን ያየነውን የጌታችንን የኢየሱስን ታላቅ ግርማዊነት አይተን እንጂ በሰዎች ድንቅ ችሎታ የተቀናበረ ታሪክ ላይ ተመሥርተን አይደለም፡፡ 17 እግዚአብሔር አባታችን በታላቅ ሞገስ ባከበረው ጊዜና የእርሱ ታላቅ ብርሃን በከበበው ጊዜ “በእርሱ በጣም ደስ የሚለኝ እጅግ የምወደው ልጄ እርሱ ነው፡፡” አለ፡፡ 18 እኛ ራሳችን ከክርስቶስ ጋር በዚያ ቅዱስ ተራራ ላይ አብረን በነበርን ጊዜ እግዚአብሔር ይህንን ከሰማይ ሲናገር ሰምተነዋል፡፡ 19 በዚህ መንገድ ላየነው ነገር ምክንያት የሆነው ነቢያት ከብዙ ዘመናት በፊት ስለ ክርስቶስ የጻፉት ሙሉ በሙሉ የሚታመን መሆኑን በይበልጥ አረጋግጠናል፡፡ በጨለማ የሚያበራ ብርሃን ሰዎች የሚሄዱበትን መንገድ በግልጽ እያሳየ እንደሚረዳቸው እኛም ያስተማርናችሁ ነገር እውነት ወይም ውሸት እንደሆነ ማረጋገጥ እንድትችሉ ከሌላው ጊዜ ይልቅ ትኩረት ሰጥታችሁ ነቢያቱ ስለጻፉት ነገር አንብቡ፡፡ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ መጥቶ እግዚአብሔርን በሙላት ማወቅ እስኪያስችላችሁ ድረስ ስላጻፉት ነገር ትኩረት ስጡ፡፡ በዚያም ወቅት ጎህ ሲቀድና የንጋት ኮከብ ሲያበራ እንደሚሆነው በእንደዚያ ዓይነት መልክ አጥርተን ማየት እንችላለን፡፡ 20 ማንም ነቢይ ያለ እግዚአብሔር መንፈስ እርዳታ በመጽሐፍ የተጻፉትን የትንቢት ቃላት መተርጎም እንደማይችል ልትገነዘቡ ይገባችኋል፡፡ 21 ምክንያቱም ማንም ሰው በፍላጎቱ እነዚያን ትንቢቶች አልተናገርምና ነው፡፡ ከዚያ በተቃራኒው ከእግዚአብሔር መልእክትን የሚናገሩ ያን የተናገሩት በእግዚአብሔር መንፈስ እርዳታ ነው፡፡ ስለዚህም እኛም የተናገሩትን እንድንረዳ መንፈስ ቅዱስ ሊያግዘን ግድ ነው፡፡