1 እናንተ ሁላችሁም በሽማግሌነቴ ታውቁኛላችሁ፡፡ ይህን ደብዳቤ ለእናንተ ለአማኞችና በጣም ለምወደው የአማኞች ጉባኤ እጽፋለሁ፡፡ እግዚአብሔር እናንተን መርጧችኋል፤ እኔም እወዳችኋለሁ ምክንያቱም እኛ ስለ ክርስቶስ የምናውቀው እውነት ነው! የምወዳችሁ እኔ ብቻ አይደለሁም፣ ነገር ግን ኢየሱስ ያስተማራቸውን ዕውነተኛ ትምህርቶች የተቀበሉ ሁሉ ይወዷችኋል! 2 ይህም ሁላችንም የእግዚአብሔርን እውነተኛ መልዕክት ስላመንን ነው፡፡ ይህ በውስጣችን ነው፤ ደግሞም ይህን ለዘለዓለም ማመናችንን እንቀጥላለን! 3 እግዚአብሔር አብ እና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ በመልካምነቱና መህረቱ ማድረጉን ይቀጥላል ምክንያቱም እርሱ ይወደናል፡፡ እነርሱ ሰላም እንዲኖረን ያስችሉና፣ ምክንያቱም እነርሱ በእውነት እኛን ይወዱናል፡፡ 4 አንዳንዶቻችሁ እግዚአብሔር ባስተማረን ዕውነት መሰረት እየኖራችሁ እንደሆነ ስላወቅሁ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ይህም ልክ አባታችን እንዳዘዘን ነው፡፡ 5 እናም አሁን፣ የተወደዳችሁ አማኞች ሆይ፣ እርሱ እንዲናደርገው ያዘዘንን እንድትታዘዙ እለምናችኋለሁ፡፡ የምጽፍላችሁ ለዚህ ነው፡፡ እርሱ እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ያዘዘው አዲስ ትዛዝ አይደለም፤ይልቁንም እርስ በእርሳችን መዋደድ እንዳለብን ያወቅነው በመጀመሪያ በክርስቶስ ባመንን ጊዜ ነበር፡፡ 6 እግዚአብሔርን መውደድና እርስ በእርሳችንም መዋደድ ማለት ይህ ነው፤ እግዚአብሔር እንድናደርገው ያዘዘንን ማድረግ አለብን፡፡ እርሱ እንድናደርገው ያዘዘን እርሱን እንድንወድና እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ነው፡፡ 7 ሌሎችን የሚያታልሉ ብዙ ሰዎች ከእናንተ ጉባኤ ተለይተው ወጥተዋል እናም ከእናንተ አካባቢ ወጥተው ወደ ሌሎች ሄደዋል፡፡ እነርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው እንደሆነ የማይቀበሉ ናቸው፡፡ ሌሎችን የሚያታልሉና ክርስቶስን የሚቃወሙ ናቸው፡፡ 8 ስለዚህ እነዚያ አስተማሪዎች እንዳያታልሏችሁ ተጠንቀቁ! እንዲታልሏችሁ ከተዋችኋቸው፣ እኛ ከእናንተ ጋር ሽልማት ለማግኘት ስንሰራ የነበርንበትን ታጣላችሁ፣ ደግሞም ከእግዚአብሔር ጋር ዘለዓለማዊ ህብረት በማድረግ የምትቀበሉትን የተሟላ ሽልማት አትቀበሉም! 9 ክርስቶስ ያስተማረውን የሚለውጡና እርሱ ያስተማረውን በማመን የማይቀጥሉ ከእግዚአብሔር ጋር ህይወት የላቸውም፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ ያስተማረውን በማመን የሚቀጥሉ ከአባታችን ከእግዚአብሔር አብ ጋር እና ከልጁም ጋር ህብረት አላቸው፡፡ 10 ስለዚህ ክርስቶስ ካስተማረው የተለየ ነገር የሚያስተምር ማንም ወደ እናንተ ሲመጣ፣ ቤታችሁ አትቀበሉት! ሰላምታ በመስጠት ወይም ለእርሱ በጎነት በመመኘት በማናቸውም መንገድ አታበረታቱት! 11 ይህን የምናገረው ወገኖችን እንደምትቀበሉ አድርጋችሁ ሰዎችን እንደዚያ ብታስተናግዷቸው ክፉ ተግባራትን እንዲሰሩ እየረዳችኋቸው ነው ማለት ነው፡፡ 12 ሌላ ልነግራችሁ የምፈልጋቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩኝም፣ ይህንን በደብዳቤ ላለመግለጽ ወስኛለሁ፡፡ በዚህ ምትክ፣ በቶሎ ከእናንተ ጋር ለመገናኘትና ፊት ለፊት ለመነጋገር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከዚያ አብረን ሙሉ ደስተኞች ልንሆን እንችላለን፡፡ 13 እግዚአብሔር የመረጣቸው እዚህ ያሉ አማኝ ወገኖቻችሁ ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፡፡