1 እኔ ጳውሎስ ከክርስቲያን ወንድማችን ከጢሞቴዎስ ጋር በመሆን ይህን መልእክት ጻፍንላችሁ፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ እንዳገለግለውና ለእግዚአብሔር ፈቃድ እንድታዘዝ ላከኝ፡፡ ይህን መልእክት የምንልከው የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነው በቆሮንቶስ ከተማ ለተሰበሰቡ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለራሱ ለለያቸው - በአካይያ ክፍለ አገር ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ሁሉ ነው፡፡ 2 እግዚአብሔር ነጻ ስጦታዎቹን ፍቅሩንና ሰላሙን ይሰጣችሁ፣ እነዚህ ነገሮች ከአባታችን ከእግዚአብሔር ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣሉ፡፡ 3 በርኅራኄው የሚጎበኘንንና ሁልጊዜ የሚያጽናናንን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ሁልጊዜ እናመሰግናለን፡፡ 4 በማንኛውም ስቃይ ባለበት መከራ ውስጥ ስናልፍ እግዚአብሔር ያጽናናል፡፡ መከራ እየተቀበሉ ላሉ ለሌሎች ሰዎች ያንኑ መጽናናት እናካፍል ዘንድ የእርሱ ማጽናናት ሕይወታችንን ይፈውሰዋል፡፡ 5 ከመጠን በላይ የሆነውን የክርስቶስን መከራ እንደምንካፈል ሁሉ በክርስቶስ አማካይነት ሊለካ የማይችለውን መጽናናት እንካፈላለን፡፡ 6 ምን ጊዜም መከራ የምንቀበለው እግዚአብሔር እንዲያጽናናችሁና ከአደጋም እንዲያድናችሁ ነው፡፡ ምን ጊዜም እግዚአብሔር የሚያጽናናን እኛ መከራ በምንቀበልበት መንገድ መከራን በምትቀበሉበት ጊዜ፣ ከፊት ይልቅ እንድትጽናኑና እግዚአብሔርን መጠበቅን ሊያስተምራችሁ እንዲችል ነው፡፡ 7 ለእናንተ ስለሚሆንላችሁ ነገር እርግጠኞች ነን፣ ምክንያቱም እኛ መከራ እንደምንቀበል መከራ ስለምትቀበሉ፣ እኛን እንዳጽናናን ያጽናናችኋል፡፡ 8 በክርስቶስ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሆይ! በእስያ ክፍለ አገር ስለነበረብን መከራ እንድታውቁ እንፈልጋለን፡፡ መከራው ልንታገሠው ከምንችለው በላይ ስቃይ አደረሰብን፡፡ እንሞታለን ብለን ተስፋ ቆርጠን ነበር፡፡ 9 የሞትን ፍርድ አስተላልፈውብን ነበር፣ መገደላችንንም ስንጠበቅ ነበር፡፡ ያ የሞት ፍርድ ሙታንን በሚያሥነሣና መልሶ ሕያዋን በሚያደርጋቸው በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን ብርታት እንዳንደገፍ አስተምሮናል፡፡ 10 ነገር ግን እግዚአብሔር ከእነዚያ አሰፈሪ አደጋዎች አዳነን፣ ወደፊትም እንደሚያድነን ተስፋን ሰጠን፡፡ 11 ስለ እኛ በመጸለይ በደገፋችሁን መጠን ይህን ያደርግልናል፡፡ ብዙዎች ስለጸለዩልን፣ እርሱም በጣም ስለራራልን ብዙዎች አሁን እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፡፡ 12 ከሰዎች ሁሉ ጋር በታማኝነትና በቅንነት እንደኖርን በሙሉ ደስታ መናገር እንችላለን፡፡ በዓለም እንደ እግዚአብሔር እንደራሱ ሕዝብ ኖርን፣ ደግሞም በእግዚአብሔር ላይ ጥልቅ የሆነ እምነት አለን፤ ይኼውም የእርሱ ሥጦታ ነበር፡፡ በየትኛውም የዓለም ሚዛን አንኖርም፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብን በምንመርጥበት ጊዜ የዓለምን ጥበብ አናደምጥም፡፡ በዚያ ፈንታ፣ እንዴት መኖር እንዳለብን እግዚአብሔር ታማኞችና ቅዱሳን አድርጎናል፡፡ 13 መልእክቶቼን አንብባችኋል፡፡ ልትረዷቸው በምትችሉበት ሁኔታ ጻፍኳቸው፡፡ 14 አሁን ስለ እኛ ጥቂት ታውቃላችሁ፣ ነገር ግን ጌታ ኢየሱስ በሚመለስበት ቀን፣ በፊቱ በጣም እንደምትመኩብን ተስፋ አደርጋለሁ፣ እኛም በእናንተ እንመካለን፡፡ 15 ሁለት ጊዜ ልጎበኛችሁ እንደምችል እርግጠኛ ስለነበርኩ በመጀመሪያ ወደ እናንተ ልመጣ ፈልጌ ነበር፡፡ 16 ወደ መቆደንያ ስሄድና ከዚያም ስመለስ ሁለት ጊዜ ላያችሁ፣ ወደ ይሁዳም በማደርገው ጉዞ እንድትረዱኝ አሰብኩ፡፡ 17 በአእምሮዬ የነበረው እቅድ ይህ ነበር፡፡ “አዎን” ብዬ ነግሬአችሁ ቀጥሎ “አይደለም” ብዬ እየነገርኳችሁ አይደለም፡፡ የማያምኑ ሰዎች ብዙ ጊዜ እንደሚያቅዱት እያቀድኩ አልነበረም፡፡ 18 ነገር ግን እኛን በሚመራበት አመራሩ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ እኛም ግራ አናጋባችሁም፡፡ እናቅዳለን ደግሞም በእቅዳችን እንቆማለን፡፡ 19 የእኛ “አዎ” ካወጀንላችሁ ከእግዚአብሔር ልጅ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ የሆነ ነው፤ በእርሱም ምንም ዓይነት ግራ መጋባት የለም - በእርሱ ዘንድ “አዎን” ብሎ በመቀጠል “አይደለም” የለም፡፡ ይልቁን ሁልጊዜ በእርሱ “አዎን” ነው፡፡ 20 የእግዚአብሔር ተስፋዎች “አዎን” ናቸው፡፡ ምክንያቱም ከእርሱ የተሰጡ ናቸው፡፡ 21 ሁለታችንም ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆናችን ምክንያት እግዚአብሔር በእኛ በክርስቲያኖች መካከል ያለውን ኅብረት ጠንካራ አድርጎታል፣ የምሥራቹንም ቃል ለሰዎች እንድንነግር የላከን እርሱ ነው፡፡ 22 የተቀበለን መሆኑን ሰዎች ያውቁ ዘንድ ሕጋዊ ማኅተሙን በላያችን አሳረፈ፡፡ ደግሞም ወደፊት የሚበልጡ ነገሮችን እንኳን እንደሚያደርግልን የሰጠን ተስፋ እንደማይታጠፍ ሊያረጋግጥልን በውስጣችን የሚኖር መንፈሱን ሰጠን፡፡ 23 በቆርንቶስ የምትገኙ ክርስቲያኖች ሆይ! ወደ እናንተ ያልመጣሁበትን ምክንያት እግዚአብሔር ራሱ ያሳያችሁ፣ እርማት ስሰጣችሁ ፊት ለፊት እየተመለከትኳችሁ እንዳይሆን በማሰብ ነበር፡፡ 24 እኛ በእግዚአብሔር እንዴት መታመን እንዳለባችሁ ትእዛዝ እንደሚሰጡ አለቆች አይደለንም፡፡ ነገር ግን፣ ምንም ቢሆን በእግዚአብሔር መታመንን መማር እንድትችሉና በእርሱ በመታመን ደስተኞች እንድትሆኑ አብረናችሁ ልንሰራ እንፈልጋለን፡፡