ምዕራፍ 1

1 አምላኩ ያህዌ ከእርሱ ጋር ስለ ነበርና ኀያል ንጉሥ እንዲሆን ስለ ረዳው፣ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን መንግሥቱ ጸንቶለት ነበር፡፡ 2 3 4 5 ዳዊት በነገሠ ጊዜ በኢየሩሳሌም ለሚሠራው አዲስ ቤተ መቅደስ የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ከዚያም ዳዊትና የእስራኤል መሪዎች ከቂርያት ይዓሪም ከተማ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ አዲሱ ቅዱስ ድንኳን አመጡ፡፡ ነገር ግን ሰሎሞን በነገሠ ጊዜ የመጀመሪያው ቅዱስ ድንኳን ገና በገባዖን ከተማ እንዳለ ነበር፡፡ የዑሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው የናሱ መሠዊያም በገባዖን ባለው የመጀመሪያው ድንኳን ፊት ነበር፡፡ ሰሎሞን የሰራዊቱን ሻለቆችና መቶ አለቆች፣ ዳኞችንና ሌሎች የእስራኤል መሪዎችን በሙሉ በአንድነት ጠራ፡፡ ከእርሱ ጋር ወደ ገባዖን እንዲሄዱ ነገራቸው፤ እነርሱም ከእርሱ ጋር ጣዖቶች ወደሚመለኩበት በገባዖን ኮረብታ ወዳለ ቦታ ሄዱ፡፡ ይህ ቦታ ሙሴ በተከለው ድንኳን እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ይገናኝ የነበረበት ቦታ ነበር፡፡ በዚያም ሰሎሞንና ሌሎቹ ሰዎች ሁሉ ወደ ያህዌ ጸለዩ፡፡ 6 ከዚያም ሰሎሞን ታቦቱ ፊት ወዳለው የናስ መሠዊያ ሄዶ አንድ ሺህ እንስሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጐ አቀረበ፡፡ 7 በዚያ ሌሊት እግዚአብሔር በሕልም ለሰሎሞን ተገልጦ፣ ‹‹እንድሰጥህ የምትፈለገውን ሁሉ ጠይቀኝ›› አለው፡፡ 8 ሰሎሞንም እንዲህ በማለት መለሰ፣ ‹‹አንተ ለአባቴ ለዳዊት እጅግ ቸር ነበርህ፤ አሁን ደግሞ እኔን ቀጣዩ ንጉሥ አደረግኸኝ፡፡ 9 አምላኬ ያህዌ ሆይ፣ እንደ የምድር ትቢያ ብዛት ያለው ሕዝብ ንጉሥ አድርገኸኛል፤ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸውን ቃል ፈጽም፡፡ 10 ያለ አንተ ርዳታ ይህን የሚያህል ታላቅ ሕዝብ ማስተዳደር እንድችል እባክህን ጥበበኛ አድርገኝ›› አለ፡፡ 11 እግዚአብሔርም እንዲህ በማለት ለሰሎሞን መለሰለት፤ ‹‹ብዙ ገንዘብ፣ ክብር ወይም የጠላቶችህን ሞት አልለምንህም፤ ረጅም ዘመን በሕይወት መኖርንም አልለመንህም፤ ይልቁንም እኔ በሾምሁህ ሕዝብ ላይ በትክክል ማስተዳደር የሚያስችልህን ጥበብ እንድሰጥህ ለምነኸኛል፡፡ 12 ስለዚህ እኔ ጥበብንና ሕዝቤን ማስተዳደር የምትችልበትን ዕውቀት እሰጥሃለሁ፡፡ እጅግ ብዛት ያለው ሀብትንና ከአንተ በፊት ከነበሩትም ሆነ፣ ከአንተ በኃላ ከሚመጡት ንጉሦች የበለጠ በየትኛውም አገር ያሉ ሰዎች እንዲያከብሩህ አደርጋለሁ፡፡›› 13 ከዚያም ሰሎሞንና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች በገባዖን ከነበረው የተቀደሰ ድንኳን ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በዚያም የእስራኤልን ሕዝብ ማስተዳደር ጀመረ፡፡ 14 ሰሎሞን አንድ ሺህ አራት መቶ ሰረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት፡፡ ከሰረገሎቹና ከፈረሶቹ የተወሰኑትን በኢየሩሳሌም፣ የተቀሩንም በተለያዩ ከተሞች አኖረ፡፡ 15 ሰሎሞን ንጉሥ በነበረበት ዘመን በኢየሩሳሌም ብርና ወርቅ እንደ ተራ ድንጋይ የበዛ ነበር፤ ዝግባውም በየኮረብታው ግርጌ እንደሚገኝ የሾላ ዛፍ እንጨት የበዛ ነበር፡፡ 16 የሰሎሞን ፈረሶች ከግብፅና ቱርክ ውስጥ ካለው ቀዌ የመጡ ነበሩ፡፡ 17 የሰሎሞን ሰዎች ለአንድ ሰረገላ ሰባት ኪሎ ግራም ወርቅ ለአንድ ፈረስ አንድ እና ሰባት ዐሥረኛ ኪሎ ግራም ብር ለግብፅ ከፍለዋል፡፡ ከእነርሱም ብዙዎቹን ለኬጢያውያንና ለሶርያውያን ነገሥታት ሸጠውላቸው ነበር፡፡