1 እኔ ጳውሎስ ይህንን መልእክት የጻፍኩት ለጢሞቴዎስ ነው፡፡ ከአዳኛችን ከእግዚአብሔርና ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሳ ለወደፊት የጸና ተስፋ አለን፣ ክርስቶስ ደግሞ የእርሱ ሐዋርያ እንድሆን አዘዘኝ፡፡ 2 አንተ እውነተኛ ልጄ ነህ ምክንያቱም በጌታ እንድታምን የመራሁህ እኔ ነኝ፡፡ ከእግዚአብሔር ከአባታችን እንደዚሁም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ይብዛልህ፣ ምህረትን ያብዛልህ፣ ሰላምንም ይስጥህ፡፡ 3 እኔ ወደ መቄዶንያ ስሄድ አንተ በኤፌሶን እንድትቆይ አጥብቄ የለመንሁህ እኛ ከምናስተምረው ትምህርት ጋር የማይስማማ ትምህርት እንዳያስተምሩ አንዳንድ ሰዎችን እንድታዛቸው ፈልጌ ነው፡፡ 4 በተጨማሪ ሰዎች ለምንም ለማይጠቅም ተረትና መጨረሻ ለሌለው የትውልዶች ታሪክ ጊዜአቸውንና ራሳቸውን እንዳይሰጡ እዘዛቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲከራከሩ የሚያደርጉ ናቸው፤ ይሁን እንጂ በእምነት የሆነውን የእግዚአብሔርን ስራ ማለትም እኛን የማዳን እቅድ እንዲያውቁ ፈጽሞ አያግዛቸውም፡፡ 5 እኛ ለአንተ ይህንን ትዕዛዝ የሰጠንህ ሰዎች እግዚአብሔርን በንጹህ ልብ፣ በመልካም ህሊና እና እውነተኛ በሆነ እምነት እንዲወዱት እንድታስተምራቸው በማሰብ ነው፡፡ 6 አንዳንድ ሰዎች እነዚህን መልካም የሆኑትን ነገሮች ማድረግ ትተዋል፤ ይልቁንም አሁን የማይጠቅሙ ከንቱ ነገሮችን እየተናገሩ ነው፡፡ 7 ስለ ሕግ ማስተማር ይፈልጋሉ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸው ሕጉ አልገባቸውም፡፡ እንዲህም ሆኖ እነርሱ የሚያስተምሩት ትምህርት እውነት እንደሆነ ለማሳመን ይከራከራሉ፡፡ 8 ነገር ግን እኛ ሕጉ እንደሚናገረው እንዴት እንደምንጠቀምበት የምናውቅ ከሆነ ሕግ መልካም እንደሆነ እናውቃለን፡፡ 9 ሕጉ መልካም የሆኑ ሰዎችን ለመቆጣጠር እንዳልተሰጠ እናውቃለን፤ ነገር ግን ሕግ የተሰጠው አመጸኛ እና እግዚአብሔርን የማያከብሩ ሰዎች፣ ኃጢአተኞች እና ሰዎችን የማያከብሩ፣ የራሳቸውን ወላጆች ጭምር የሚገድሉ ነፍሰ ገዳዮችን ለመቆጣጠር ነው፡፡ 10 ከዚህ በተጨማሪ ሕግ የተሰጠው በተመሳሳይ ጾታ መካከል ለግብረሰዶማውያንና በተፈጥሮ ከተቀበሉት ባህርያቸው ውጭ ወሲብን ለሚፈጽሙ፣ ሰዎችን ለሚሰርቁና ባሪያ አድርገው የሚሸጡትን፣ ውሸተኞችን እና በፍርድ ቤት ፊት በሐሰት የሚመሰክሩትን ለመቆጣጠር ነው፡፡ እንዲሁም ሕግ የተሰጠው እኛ ከምናሰተምረው መልካምና ጤነኛ ትምህርት የተለየ ማንኛውንም ትምህርት ለማስቆም ነው፡፡ 11 ይህ እኛ የምናስተምረው ጤናማ ትምህርት የምናከብረው አምላካችን እግዚአብሔር ካስተማረን ትምህርትና ለሌሎች እሰብከው ዘንድ በአደራ ከሰጠኝ አስደናቂ ወንጌል ጋር የሚስማማ ነው፡፡ 12 እርሱን እንዳገለግለው ብርታት ስለሰጠኝ ጌታችንን ክርስቶስ ኢየሱስን አመሰግናለሁ፡፡ እርሱን ለማገልገል ብቁ እንደሆንሁ በመቁጠር ሾመኝ፡፡ 13 ባለፉት ዘመናት አማኞችን ተሳድቤአለሁ ደግሞም አሳድጄአለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አመጽ የተሞላ ድርጊት ፈጽሜአለሁ፣ ነገር ግን ይህን ያደረግሁት ባለማመንና ባለማወቅ ስለነበር እግዚአብሔር ምህረት አደረገልኝ፡፡ 14 እግዚአብሔር ለእኔ ምህረቱን አትረፍርፎ አበዛልኝ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው እምነትና ፍቅር ከእርሱ ጋር ሕብረት እንዲኖረኝ በማድረግ ጸጋ አበዛልኝ፡፡ 15 ይህንን እውነት ሁሉም ሰው ሊቀበለው ይገባል ምክንያቱም ሙሉ በሙሉ የታመነ ስለሆነ ነው፡- ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ኃጢአተኞችን ለማዳን ነው፡፡ ከኃጢአተኞችም ሁሉ ዋና እኔ መሆኔ የማይታበል እውነት ነው፡፡ 16 ነገር ግን የኃጢአተኞች ዋና እኔ ስለሆንሁ ከሁሉም ሰው በፊት እግዚአብሔር ለእኔ እጅግ ብዙ ምህረት አደረገልኝ፤ ይህንን ያደረገው ደግሞ ሰዎች እርሱ ምን ያህል ትዕግስተኛ እንደሆነ እንዲያውቁ ነው፡፡ አሁንም እግዚአብሔር በእርሱ ለሚያምኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ በትዕግስት እየጠበቃቸው ነው፡፡ 17 ይህ የዘላለም ንጉስ በዓይን የሚታይ አይደለም ደግሞም አይሞትም፡፡ እርሱ ብቻውን አምላክ ነው፡፡ ፍጥረት ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚያከብሩትና የሚያመሰግኑት እርሱን ነው፡፡ አሜን! 18 ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ፣ ይህን አዝሃለሁ፡- አንዳንድ አማኞች ስለ አንተ የተናገሩትን ትንቢት አስታውስ፡፡ ለጌታ የሚሆነውን አገልግሎትህን በትጋት እየፈጸምህ ሳለህ እነዚህን የተነገሩትን ነገሮች ለመከተል ትጋ፡፡ 19 በእግዚአብሔር ታመን፣ በጎ ሕሊናም ይኑርህ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ስለ በጎ ሕሊናቸው ፈጽሞ ግድ የላቸውም፡፡ ከዚህ የተነሳ እምነታቸውን አጥፍተዋል፡፡ 20 ከእነዚህም መካከል ሁለቱ ሰዎች ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዳይሳደቡ ትምህርት ያገኙ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፌ ሰጥቻቸዋለሁ፡፡