ምዕራፍ 1

1 በተራራማው በኤፍሬም አገር በራማ መሴፋ የሚኖር አንድ ሰው ነበር፤ ስሙ ሕልቃና ይባላል፥ እርሱም የኤፍሬማዊው የናሲብ ልጅ፥ የቶሑ ልጅ፥ የኤሊዮ ልጅ፥ የኢያርምኤል ልጅ ነበር። 2 እርሱም ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ ስማቸውም የአንደኛዋ ሐና፥ የሁለተኛዋም ፍናና ነበር። ፍናና ልጆች ነበሯት፣ ሐና ግን አንድም ልጅ አልነበራትም። 3 ይህም ሰው በየዓመቱ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ለመስገድና መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ሴሎ ይሄድ ነበር። የእግዚአብሔር ካህናት የሆኑት ሁለቱ የኤሊ ወንዶች ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በዚያ ነበሩ። 4 በየዓመቱ ሕልቃና የሚሠዋበት ጊዜ ሲደርስ፥ ለሚስቱ ፍናና፥ ለወንዶችና ሴቶች ልጆችዋ በሙሉ ሁልጊዜ ከመሥዋዕቱ ሥጋ ድርሻቸውን ይሰጣቸው ነበር። 5 ነገር ግን ሐናን ይወዳት ስለነበር ሁልጊዜም ድርሻዋን ሁለት ዕጥፍ አድርጎ ይሰጣት ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ማኅፀንዋን ዘግቶት ነበር። 6 እግዚአብሔር ማኅፀንዋን ዘግቶት ስለነበር ጣውንቷ እርስዋን ለማስመረር ክፉኛ ታስቆጣት ነበር። 7 ስለዚህ በየዓመቱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ከቤተሰብዋ ጋር በምትወጣበት ጊዜ ጣውንቷ ሁልጊዜ ታበሳጫት ነበር። በዚህ ምክንያት ታለቅስ ነበር፤ ምግብም አትበላም ነበር። 8 ባሏ ሕልቃና ሁልጊዜ "ሐና ሆይ፥ ለምንድነው የምታለቅሽው? ምግብስ የማትበዪው ለምንድነው? ልብሽ የሚያዝነውስ ለምንድነው? ከዐሥር ወንዶች ልጆች ይልቅ ላንቺ እኔ አልሻልም?" ይላት ነበር። 9 ከእነዚህ ወቅቶች በአንዱ፥ በሴሎ መብላታቸውንና መጠጣታቸውን ከጨረሱ በኋላ ሐና ተነሣች። ካህኑ ዔሊ በእግዚአብሔር ቤት መግቢያ በራፍ በወንበሩ ላይ ተቀምጦ ነበር። 10 እርሷም እጅግ አዝና ነበር፤ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች፥ አምርራም አለቀሰች። 11 እንዲህ ስትልም ስዕለት ተሳለች፣ "የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ የአገልጋይህን ጉስቁልና ብትመለከትና ብታስበኝ፥ አገልጋይህን ባትረሳኝ፥ ነገር ግን ወንድ ልጅን ብትሰጠኝ፥ እኔም የሕይወት ዘመኑን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፥ መቼም ቢሆን ጸጉሩ አይላጭም"። 12 በእግዚአሔር ፊት ጸሎቷን ቀጥላ እያለች ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር። 13 ሐና በልቧ ትናገር ነበር። ከንፈሮችዋ ይንቀሳቀሱ ነበር፥ ድምፅዋ ግን አይሰማም ነበር። ስለዚህ ዔሊ ሰክራለች ብሎ አሰበ። 14 ዔሊም "ስካርሽ የሚቆየው እስከ መቼ ነው? ወይንሽን ከአንቺ አርቂው" አላት። 15 ሐናም፣ "ጌታዬ ሆይ፥ አይደለም፥ እኔ ልቤ በሐዘን የተጎዳብኝ ሴት ነኝ። ወይን ወይም የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም፥ ነገር ግን ነፍሴን በእግዚአብሔር ፊት እያፈሰስኩ ነው። 16 አገልጋይህን እንደ ኃፍረተ ቢስ ሴት አትቁጠረኝ፤ ይህን ያህል ጊዜ የተናገርኩት እጅግ ከበዛው ሐዘኔና ጭንቀቴ የተነሣ ነው" በማለት መለሰችለት። 17 ከዚያም ዔሊ፣ "በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሽውን ልመና ይስጥሽ" ብሎ መለሰላት። 18 እርሷም፣ "አገልጋይህ በዐይንህ ፊት ሞገስን ላግኝ" አለችው። ከዚያም መንገዷን ሄደች፥ በላችም፤ ከዚያም በኋላ ፊቷ ሐዘንተኛ አልሆነም። 19 እነርሱም ማልደው ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፥ ከዚያም ወደ መኖሪያቸው ወደ አርማቴም ተመለሱ። ሕልቃና ከሚስቱ ከሐና ጋር ተኛ፥ እግዚአብሔርም አሰባት። 20 ጊዜው ሲደርስም ሐና አረገዘችና ወንድ ልጅ ወለደች። "ከእግዚአብሔር ስለ እርሱ ለምኜ ነበር" ስትል ስሙን ሳሙኤል ብላ ጠራችው። 21 ሕልቃናና ቤተ ሰቡ በሙሉ ለእግዚአብሔር ዓመታዊውን መሥዋዕት ለማቅረብና ስዕለታቸውን ለመፈጸም ዳግመኛ ወደ ሴሎ ወጡ። 22 ሐና ባሏን "ልጁ ጡት መጥባት እስኪያቆም እኔ አልሄድም፤ ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት እንዲታይና ለዘላለም በዚያ እንዲኖር አመጣዋለሁ" ብላው ስለነበረ አልሄደችም። 23 ባሏም ሕልቃና፥ "መልካም መስሎ የታየሽን አድርጊ። ጡት መጥባቱን እስኪያቆም ቆዪ፥ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን ያጽና" አላት። ስለዚህ ልጇ ጡት መጥባቱን እስኪያቆም ድረስ በቤት በመቆየት ተንከባከበችው። 24 ጡት መጥባቱን ባስቆመችው ጊዜ፥ እርሱን ከሦስት አመት ወይፈን፥ አንድ ኢፍ ዱቄትና አንድ ጠርሙስ ወይን ጋር በሴሎ ወደሚገኘው ወደ እግዚአብሔር ቤት ወሰደችው። ልጁ ገና ሕፃን ነበር። 25 ወይፈኑን አረዱት፤ ልጁንም ወደ ዔሊ አመጡት። 26 እርሷም፥ "ጌታዬ ሆይ፥ ሕያው እንደመሆንህ፥ እዚህ አጠገብህ ቆማ ወደ እግዚአብሔር የጸለየችው ሴት እኔ ነኝ። 27 ስለዚህ ልጅ ጸለይኩኝ፥ እግዚአብሔርም የለመንኩትን ልመና ሰጥቶኛል። 28 ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ በሕይወት በሚኖርበት ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል"። እነርሱም በዚያ ለእግዚአብሔር ሰገዱ።