ምዕራፍ 1

1 ዙፍ ከሚባለው ወገን የሆነ ተራራማ ስፍራ ላይ በምትገኝ የኤፍሬም ነገድ መኖሪያ በነበረችው ራማ ከተማ የሚኖር ሕልቃና ተብሎ የሚጠራ ሰው ነበር፡፡ ወላጅ አባቱ ኢያሬምኤል፣ አያቱ ኤሊሁ፣ ቅድመ-አያቱም ቶሁ ነበሩ፡፡ እርሱም ዙፍ የሚባለው ነገድ ወገን ነው፡፡ 2 እርሱም ሐናና ፍናና የሚባሉ ሁለት ሚስቶች ነበሩት፡፡ ፍናና ብዙ ልጆች ሲኖሯት፥ ሐና ግን ልጅ አልነበራትም። 3 በዓመት አንድ ጊዜ ሕልቃና ቤተ ሰቡን ይዞ ከራማ ወደ ሴሎ ይሄድ ነበረ፡፡ ወደዚያ የሚጓዝበት ምክንያትም መላእክት ሠራዊት አለቃ የሆነውን ጌታ እግዚአብሔርን ሊያመልክና ለእርሱም መሥዋእትን ለማቅረብ ነው፡፡ ሁለቱ የዔሊ ልጆቹ አፍኒንና ፊንሐስ በዚያ እንደ ጌታ እግዚአብሔር ካህን ሆነው የክህነት ተግባር እያከናወኑ አባታቸውን ይረዱት ነበር። 4 ሕልቃና መሥዋዕት የሚያቀርብበት ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉ ለሚስቱ ለፍናና ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ጥቂት ሥጋ የየራሳቸውን ድርሻ ይሰጣቸው ነበር። 5 ምንም እንኳ ጌታ እግዚአብሔር ልጅ መውለድ ትችል ዘንድ ባይፈቅድላትም፣ሐናን ያፈቅር ስለ ነበረ ለእርሷ ከፍተኛ መጠን ያለውን ሥጋ አስበልጦ ሰጣት፡፡ 6 በዚህም ምክንያት ሌላኛዪቱ ሚስቱ ፍናና ልጆች መውለድ እንዳትችል ጌታ እግዚአብሔር እንዳልፈቀደላት በማስታወስ ሐና ላይ ታፌዝባት፣ ታስቆጣት፣ ታበሳጫትም ነበር። 7 ይህም በየዓመቱ ይደጋገም ነበር፡፡ እነርሱም ወደ ጌታ እግዚአብሔር መቅደስ ወደ ሴሎ በተጓዙ ጊዜ፣ ፍናና ሁልጊዜ ፍናና ሃናን እጅግ ታዋርዳት ነበርና ሐና ታለቅስ እንዲሁም ምንም ዓይነት ምግብ አትቀምስም ነበር። 8 ስለዚህ ሕልቃና፦ “ሐና ሆይ፣ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ መብል መጠጥ አትቀምሺም? በጣም አዝነሻል! እንደ እውነቱ ከሆነ እኔ ባልሽ መሆኔ ለአንቺ አሥር ልጆች ከሚኖሩሽ እንኳ ይበልጣል” ይላት ነበር። 9 አንድ ዓመት ግን፣ በሴሎ ከበሉና ከጠጡ በኋላ፣ ሐና ልትጸልይ ተነሣች፡፡ ካህኑም ዔሊ በጌታ እግዚአብሔር መቅደስ የቤት በር የግራና ቀኝ ቋሚ እንጨት (መቃን) አጠገብ በተዘጋጀለት ወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር። 10 ሐናም በጌታ እግዚአብሔር ፊት ስትጸልይ ሳለ ልብዋ ተሰብሮ እያዘነች፣ጽኑ ልቅሶም አለቀሰች። 11 ስትጸልይም፦ “አቤቱ፣ የሠራዊት አለቃ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ የባሪያህን መዋረድ አይተህ ብታስታውሰኝ፣ በቸርነትህ ተመልከተህ ወንድ ልጅ መውለድ እንድችል ብትፈቅድልኝ፣ ቀሪ ዘመኑን ሁሉ ለአንተ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፣ ማንም ጸጉሩን እንዲላጭ ከቶ አይፈቀድለትም” ብላ ቃል ኪዳን ገባች። 12 በጌታ እግዚአብሔር ፊት እንዲህ መጸለይዋን ባበዛች ጊዜ የአፏን እንቅስቃሴ ይመለከት ነበር። 13 ሐና በጥሞና ስትጸልይ፤ ምንም ድምፅ አታሰማም ነበር፡፡ ዔሊም መጠጥ ወስዳ ሰክራለች ብሎ አሰበ። 14 እናም፦ “ መጠጣትን እስከ መቼ ትቀጥያለሽ? ወይን ጠጅሽን አስወግጂው!” አላት። 15 ሐናም፦ “ጌታዬ ሆይ፣ እንዲያውም አልሰከርሁም! ወይንም ይሁን ሌላ አስካሪ መጠጥ አልጠጣሁም፡፡ ልብዋ ያዘነባት ሴት ስለሆንኩ፤ ለጌታ እግዚአብሔር የሚሰማኝን ነገርሁት፡፡ 16 ለቁም ነገር እንደማትበቃ ሴት አድርገህ አትቍጠረኝ፡፡ እንደተመለከትከኝ እግዚአብሔርን ጊዜ ወስጄ መማጸኔ ውርደቴና ጭንቀቴ ስለ በዛ ነው” አለችው። 17 ዔሊም፦ “ነገሮችሽ ሁሉ እንዲቀኑ እመኝልሻለሁ፣ እኛ የእስራኤል ሕዝብ የምናልከው አምላክ የጠየቅሽውን ይስጥሽ” ብሎ ሸኛት። 18 ሐናም፦ “ባሪያህ በዓይንህ ፊት ከበሬታ ላግኝ” ብላ መለሰች፡፡ ከዚያም ወደ ቤተ ሰቧ ተመለሳ ጥቂት ነገር በላች-ጠጣችም፣ከእንግዲህም ወዲያ ፊትዋ ላይ የኀዘን ምልክት አልታየም። 19 ሕልቃናና ቤተ ሰቡም በሚቀጥለው ቀን ጀንበር ስትወጣ ተነሥተው ጌታ እግዚአብሔርን አመለኩ፣ ራማ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተመልሱ። ሕልቃናም እንደ ልማዱ ከሐና ጋር ተኛ፤ ጌታ እግዚአብሔርም ጸሎቷን መለሰ፡፡ 20 እርሷም ጸነሰች ወንድ ልጅም ወለደች፡፡ ስሙንም ሳሙኤል አለችው፣ ስሙ የሚሰጠው ስሜት በዕብራይስጥ ቋንቋ ውስጥ እንደሚገኙ ቃላት ትርጉም “በእግዚአብሔር የተደመጠ” ማለት ሲሆን፣ ይህንም ያለችበት ምክንያት “ልጅ እንዲሰጠኝ ጠይቄው ጌታ እግዚአብሔር ሰማኝ” ማለቷ ነው። 21 በቀጣዩ ዓመት ሕልቃና እንደ ልማዱ ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር የዓመቱን መሥዋዕትና የቃል ኪዳን ልዩ ስጦታውን ለእግዚአብሔር ሊያቀርብ ወደ ሴሎ ሄደ። 22 ሐና ግን ከእነርሱ ጋር አልሄደችም፡፡ ለባልዋም፦ “ሕፃኑ ምግብ መብላት እንዲጀምር ካደረግሁት በኋላ በእግዚአብሔር ፊት እንዲታይ ወደ ሴሎ እወስደዋለሁ፣ ቀሪ ዘመኑንም በዚያ ሁልጊዜ ይኖራል” አለችው። 23 ሕልቃናም፦ “ደስ ያሰኘሽን አድርጊ፥ ምግብ መመገብ እንዲጀምር እስታደርጊው ድረስ እዚሁ ሁኚ፡፡ ምኞቴም ጌታ እግዚአብሔር የገባሽውን ቃል እንድትፈጽሚ ያስችልሽ ዘንድ ነው” አላት። ሐናም ልጇ ምግብ መብላት እስኪጀምር በቤትዋ ተቀምጣ ትንከባከበው ነበር። 24 ሕጻኑ ምግብ መመገብ እንዲጀምር ካደረገችው በኋላ ምንም እንኳ ሳሙዔል ገና ታዳጊ ቢሆንም በሴሎ ወደሚገኘው የጌታ እግዚአብሔር ቤት ወሰደችው፡፡ ከእርሷና ልጇ ጋርም አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፣ ሃያ ሊትር ገደማ የሚይዝ አንድ ቁና ዱቄት፣ አንድ ስልቻ የወይን ጠጅ ወሰደች፡፡ 25 ሐናና ሕልቃና ወይፈኑንም መሥዋዕት አድርገው ካረዱትና በጌታ እግዚአብሔር መሰዊያ ላይ ካቀረቡት በኋላ፣ ልጁን ካሕኑ ዔሊ ፊት አመጡት። 26 ሐናም ፦ “ጌታዬ ሆይ፣ ታስታውሰኛለህ? ከብዙ ዓመታት በፊት ልጅ እንዲሰጣት በአንተ ፊት ቆማ ትጸልይ የነበረች ሴት እኔ ነኝ። 27 ጌታ እግዚአብሔር ልጅ መውለድ እንድችል ጸለይሁ፣እነሆ ያ ልጅ ነው! 28 ስለዚህም እኔ ደግሞ ለጌታ እግዚአብሔር አቅርቤዋለሁ፡፡ ቀሪ ዕድሜውን ሁሉ ለጌታ እግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል” አለችው። መጨረሻም ሕልቃናና ቤተ ሰቡ በዚያ ጌታ እግዚአብሔርን አመለኩ፡፡