ምዕራፍ 1

1 ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ያደረገኝ እኔ ጴጥሮስ በእርሱ ላመናችሁ ይህንን መልእክት እጽፍላችኋለሁ፤ እናንተ የራሱ እንድትሆኑ በእግዚአብሔር የተመረጣችሁ ናችሁ፡፡ ከእውነተኛ ቤታችሁ ከመንግሥተ ሰማይ በጣም ርቃችሁ በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያ እና በቢታንያ ግዛቶች፣ ለምትኖሩ እጽፍላችኋለሁ፡፡ 2 አባታችን እግዚአብሔር እርሱ ራሱ አስቀድሞ በወሰነው መሠረት መርጧችኋል፤ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንድትታዘዙ ለማድረግም የእርሱ መንፈስ ለይቷችኋል፤ ደሙም በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት እንድታገኙ አድርጓችኋል፡፡ እግዚአብሔር ቸርነቱንና ሰላሙን ያብዛላችሁ፡፡ 3 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነው እግዚአብሔር ይመስገን! ለእኛ ቸር ከመሆኑ የተነሣ እንደገና እንድንኖር አደረገን፡፡ ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ሕያው እንዲሆን ስላደረገው ለእኛ የገባውን ተስፋ እንደሚፈጽመው እናውቃለን፡፡ 4 ለዘላለም የሚኖሩትንና ለእኛ ተብለው በሰማይ የተቀመጡትን ተስፋዎች ለመቀበል እንድንጠባበቅ አስቻለን፡፡ 5 እግዚአብሔር በታላቅ ኃይሉ ኢየሱስን በማመን እንድትጸኑ ይጠብቃችኋል፡፡ አሁን ባለንበት በመጨረሻው ዘመን ከሰይጣን ኃይል ሊያድናችሁ እግዚአብሔር እየጠበቃችሁ ነው፡፡ 6 በዚያን ጊዜ ስለሚፈጸመው ነገር ደስ ይላችኋል፤ ነገር ግን አሁን በብዙ ልዩ ልዩ መከራዎች ለጊዜው እያዘናችሁ ነው፡፡ የከበሩ ማዕድናት ንጹሕ መሆናቸውን ለማየት እንደሚፈተኑት ሁሉ እናንተም እንድትፈተኑ እግዚአብሔር ፈቅዷል፡፡ እነዚህ እናንተን እየገጠሟችሁ ያሉት ፈተናዎች አስፈላጊ ናቸው፡፡ 7 እነዚህ መከራዎች የመጡባችሁ ምክንያት በኢየሱስ ላይ ያላችሁ እምነት እውነተኛ መሆኑን ለመፈተሽ ሲባል ነው፡፡ ይህ ማለት በእሳት ሊጠፋ ከሚችለው በዚህ ዓለም ካለው ወርቅ ይልቅ ለእግዚአብሔር የበለጠ ነው ማለት ነው፡፡ በኢየሱስ በማመናችሁ ምክንያት እግዚአብሔር እናንተን ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ ሲመጣ በታላቅ ክብር ያከብራችኋል፡፡ 8 ምንም እንኳን ያላያችሁት ብትሆኑም ኢየሱስን ትወዱታላችሁ፡፡ አሁን ባታዩትም እንኳ በጣም ደስ ይላችኋል፤ 9 ምክንያቱም በእርሱ አምናችኋልና እግዚአብሔር በኃጢአታችሁ ከመጣው ጥፋተኝነት እያዳናችሁ ነው፡፡ 10 እግዚአብሔር አንድ ቀን እናንተን እንዴት እንደሚያድን አሳይቷቸው ነበርና ነቢያት ከረጅም ጊዜ በፊት መልእክት ተናግረዋል፡፡ እነዚህን ነገሮች በጣም በጥንቃቄ ይመረምሩ ነበር፡፡ 11 በእነርሱ የነበረው የኢየሱስ መንፈስ ማንን እንዳመለከታቸው ለማወቅ ይፈልጉ ነበር፤ እንዲሁም መቼ እንደሆነ ጊዜውን ለማወቅ ይፈልጉ ነበር፡፡ ይህም የሆነው መንፈሱ አስቀድሞ ክርስቶስ እንደሚሠቃይና እንደሚሞት፣ ከዚያም በኋላ የከበሩ ነገሮች እንደሚሆኑለት ስለነገራቸው ነው፡፡ 12 እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች የገለጠላቸው ለእነርሱ ሲባል አለመሆኑን ነግሯቸዋል፤ ነገር ግን ለእናንተ ሲባል ነበር፡፡ ለእናንተ ይህን ያስታወቁት እግዚአብሔር ከሰማይ የላከው መንፈስ ቅዱስ ይህን እንዲደርጉ ስላስቻላቸው ነው፡፡ መላእክት እንኳ ሳይቀሩ እግዚአብሔር እኛን ያዳነበትን ይህን እውነት የበለጠ ለማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ 13 ስለዚህ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ልባችሁን አዘጋጁ፡፡ ይህም ሲባል አስተሳሰባችሁን መግራት አለባችሁ ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ በሚመለስበት ጊዜ እግዚአብሔር በቸርነቱ የሚሰጣችሁን መልካም ነገሮች እንደምትቀበሉ ሙሉ እምነት ይኑራችሁ፡፡ 14 በዚህ ምድር ላይ ሕፃናት ለወላጆቻቸው መታዘዝ እንዳለባቸው ሁሉ እናንተም ለሰማዩ አባታችሁ መታዘዝ ስለሚኖርባችሁ ስለ እግዚአብሔር እውነቱን ሳታውቁ በፊት ልታደርጉ የምትመኟቸውን ክፉ ተግባሮች አትፈጽሙ፡፡ 15 በዚያ ፈንታ የእርሱ እንድትሆኑ የመረጣችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም በምታደርጉት ነገር ሁሉ ቅዱሳን መሆን አለባችሁ፡፡ 16 በመጽሐፍ “እኔ ቅዱስ እንደሆንሁ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ብሎ እግዚአብሔር ተናግሯል ተብሎ ስለተጻፈ ቅዱሳን ሁኑ፡፡ 17 እያንዳንዱ ሰው ላደረገው ነገር ፈራጁ እግዚአብሔር ነው፤ እርሱ ደግሞ የሚፈርደው በትክክል ነው፡፡ እናንተ እርሱን ‹አባት› ብላችሁ እንደጠራችሁት በዚህ ምድር ስትኖሩ የምታሳዩት ባሕርይ የተስተካከለ ይሁን፡፡ በሰማይ ከሚገኘው ከእውነተኛ ቤታችሁ ርቃችሁ እየኖራችሁ ስለሆነ ከቤታቸው እንደተሰደዱ ሰዎች ዓይነት ናችሁ፡፡ 18 እግዚአብሔር የገዛችሁ ለዘላለም በማይኖሩት ወርቅና ብር ዓይነት ነገሮች እንዳልሆነ ታውቃላችሁና አኗኗራችሁ እርሱን በማምለክ ይሁን፡፡ ስለዚህም ከዘር ማንዘራችሁ እንደተማራችሁት ዓይነት ያለውን የሞኝነት ጠባይ ማቆም ችላችኋል፡፡ 19 ይልቁንም እናንተ የተገዛችሁት ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ ከሰውነቱ በፈሰሰው የከበረ ደሙ ነው፡፡ የአይሁድ ካህናት ይሠዉአቸው እንደነበሩት በጎች ሁሉ ክርስቶስ ምንም እንከን የሌለበት ንጹሕ ነበረ፡፡ 20 እርሱ ይህን እንዲያደርግ እግዚአብሔር የመረጠው ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን የዓለም መጨረሻ በተቃረበበት ወቅት እግዚአብሔር ለእናንተ ገለጠው፡፡ 21 ክርስቶስ ካደረገው ነገር የተነሣ እርሱን ከሞት እንዲነሣ ባደረገውና ታላቅ ክብርም በሰጠው በእግዚአብሔር አምናችኋል፡፡ ከዚህ የተነሣም ታላላቅ ነገሮችን እንደሚያደርግላችሁ እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው፡፡ 22 ስለ እግዚአብሔር የሆነውን እውነት በመታዘዛችሁ፣ እርሱም እናንተን ስላነጻችሁና አማኞችን ሁሉ እንድትወዱ ስላደረጋችሁ እርስ በርሳችሁ በቅንነትና በእውነት መዋደዳችሁን ቀጥሉ፡፡ 23 ይህንን የምጠይቃችሁ በአዲስ ሕይወት እየኖራችሁ ስለሆነ ነው፡፡ ይህንን አዲስ ሕይወት የተቀበላችሁት በሚጠፋ ነገር አማካኝነት አይደለም፤ ይልቁንስ ለዘላለም በሚኖር ነገር አማካኝነት ነው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር የተናገረውን በማመን ነው፡፡ 24 ይህ እውነት እንደሆነ እናውቃለን፤ ምክንያቱም ነቢዩ ኢሳይያስ እንደጻፈው፡- “ሳር እንደሚደርቀው ሁሉ ሰዎች በሙሉ ይጠፋሉ፡፡ የሰዎች ታላቅነትም ለዘላለም አይኖርም፤ ልክ የሳር አበባ ረጅም ጊዜ እንደማይዘልቀው ሁሉ፡፡ ሳሩ ይደርቃል፣ አበባውም ይረግፋል፤ 25 ነገር ግን የእግዚአብሔር መልእክት ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፡፡” ይህ ጸንቶ የሚኖረው መልእክት ስለ ክርስቶስ የሰበክናችሁ መልእክት ነው፡፡